ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሩሲያ የአውሮፓ ኅብረት ፕሬዝዳንትን የያዘ አውሮፕላን ጂፒኤስ ማስተጓጎሏ ተገለፀ
የአውሮፓ ኅብረት ፕሬዝዳንት የሆኑት ኧርሰላ ቫን ደር ላይንን የያዘ አውሮፕላን ጂፒኤስ በሩሲያ ባለሙያዎች መስተጓጉሉን ኮሚሽኑ አስታወቀ።
የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ እሁድ ዕለት ፕሬዝዳንቷ በደቡብ ቡልጋሪያ በማረፍ ላይ ሳሉ "የጂፒኤስ ማወክ" እንደገጠማቸው ጠቅሰው፤ ሆኖም በሰላም ማረፍ መቻላቸውን ተናግረዋል።
"ከቡልጋሪያ ባለሥልጣናት የተሰጠን መረጃ በሩሲያ የተደረገ ግልፅ ጣልቃ ገብነት መሆኑ ጥርጣሬ አለ" ብለዋል።
ፋይናንሺያል ታይምስ በስም ያልጠቀሳቸውን ባለሥልጣናት ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው የፕሬዝዳንት ኧርሰላ ቫን ደር ላይን አውሮፕላን አብራሪዎች የወረቀት ካርታ በመጠቀም በፕሎቭዲን አየር ማረፊያ አርፏል።
የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን "ዛቻ እና ማስፈራሪያ የሩሲያ አፍራሽ እርምጃ የተለመደ አካል ነው" ያለ ሲሆን፤ ድርጊቱ የመከላከያ አቅማችንን እንድናጠናክር እና ዩክሬንን እንድንደግፍ የገባነውን ቁርጠኝነት ያበረታታል ብሏል።
ድርጊቱን ተከትሎ የኅብረቱ የመከላከያ ኮሚሽነር አንድሪየስ ኩቢሊየስ የአውሮፓ ኅብረት የጂፒኤስን ጣልቃ ገብነት የሚለይ ተጨማሪ ሳተላይት ወደ ዝቅተኛው የምድር ምህዋር እንደሚልክ ተናግረዋል።
የቡልጋሪያ መንግሥት በበረራው ወቅት ወደ አውሮፕላኑ የዳሰሳ ስርዓት መረጃ ሲያደርስ የነበረው ሳተላይት ከአገልግሎት ውጭ ሆኖ እንደነበር አረጋግጧል።
የአገሪቱ መንግሥት ባወጣው መግላጫ የበረራውን ደኅንነት ለማጠበቅ የአየር ቁጥጥር አገልግሎት የምድር አሰሳ መሳሪያዎችን በመጠቀም አፋጣኝ አማራጭ ማቅረቡን ገልጿል።
የክረምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ለፋይናንሺያል ታይምስ መረጃው "የተሳሳተ ነው" ብለዋል።
የቡልጋሪያ አየር ትራፊክ አገልግሎት ባለሥልጣን ሩሲያ እ.አ.አ የካቲት 2022 በዩክሬን ወረራ ከፈፀመች ወዲህ ከጂፒኤስ ጋር የተያያዙ ክስተቶች መጨመራቸውን እንደተመለከተ ተናግሯል።
በባልቲክ ዳርቻ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የማወክ ክስተቶች መፈፀማቸውን አየር መንገዶች ሪፖርት አድርገዋል።
ሦስቱ የባልቲክ አገራት ላሪቪያ፣ ሉቲኒያ እና ኢስቶኒያ የኔቶ አባል አገራት ናቸው።
ሞስኮ በንግድ በረራዎች ጣልቃ ገብነቶችን እና ጥቃቶችን በሚመለከት የሚቀርብባትን ክስ በተጋጋሚ የካደች ሲሆን፤ እስካሁን እየጨመረ ያለው የጂፒኤስ ማወክን ከሩሲያ ጋር ያገናኘ የተረጋገጠ ማስረጃ አልቀረበም።
ይሁን እንጂ የአውሮፓ መንግሥታት እና ባለሙያዎች ስርዓትን እና የአውሮፓን ደኅንነት ለማወክ የክሬምሊን ስልት ነው በሚል በተደጋጋሚ ሩሲያን ይከሳሉ።
ምንም እንኳ አውሮፕላኖች ከጂፒኤስ ስርዓት ባሻገር ዳሰሳቸው በሌሎች መንገዶች ላይም የተመሠረተ ቢሆንም፤ በበረራ መሀል የሚፈፀም ማወክ የመከስከስ ስጋትን የሚጨምር ነው።
በአደጋው አውሮፕላኑ ከሌሎች አውሮፕላኖች ጋር መጋጨት አሊያም ከአብራሪው ቁጥጥር ውጭ ወደ መሬት፣ ውሃ እና ሌሎች አካላት ላይ ሊከሰከስ ይችላል።
የአውሮፓ ኅብረት ፕሬዝዳንት የሆኑት ኧርሰላ ቫን ደር ላይን የመከላከያ ዝግጁነትን በሚመለከት ለመወያየት በምሥራቅ አውሮፓ ይፋዊ የጉዟቸው አካል የሆነችን ቡልጋሪያን እየጎበኙ ነበር።