ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች ላይ ከፍተኛ የአየር ድብደባ ስትፈጽም፤ ኪየቭ የሞስኮን ነዳጅ ማጣሪያዎች አጠቃች

ኪየቭ የሩስያ የነዳጅ ማጣሪያዎችን ስትደበድብ ሩሲያ በበኩሏ በ14 የዩክሬን ክልሎች ላይ ከባድ ጥቃት ፈፀመች።

እንደ ዩክሬን ባለሥልጣናት መረጃ ከሆነ በሩሲያ ጥቃት በደቡባዊ ዛፖሪዝሂያ ክልል አንዲት ሴት ስትገደል ሕጻናትን ጨምሮ 30 ሰዎች ቆስለዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሩሲያ 540 የሚጠጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን እና 45 ሚሳዔሎችን ማስወንጨፏን ገልጸው ሞስኮ ላይ አዲስ ጠንካራ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል።

ምንም እንኳ ሩሲያ ስላደረሰችው ጥቃት ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ ባይቻልም የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ሁሉም "የጥቃቱ ዒላማዎች ተሳክተዋል" እንዲሁም "ዒላማ የተደረጉት አካላት ተመትተዋል" ብሏል።

ሩሲያ መጠነ ሰፊ ጥቃት የከፈተችው በሁለቱ ተፋላሚ አገራት መካከል የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ዓለም አቀፍ ጥረት እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።

የዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ሁለተኛው ትልቁ የአየር ጥቃት ነው የተባለን ድብደባ ያስተናገደች ሲሆን እስካሁን 25 ሰዎች መሞታቸው ተገልጿል።

በደቡብ ምሥራቅ ዲኒፕሮፔትሮቭስክ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ሰርሂ ሊሳክ፣ ሌሊቱን "ግዙፍ" ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና ሚሳኤሎች በመሠረተ ልማት ተቋማት ላይ በርካታ ጥቃቶችን መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

ሊሳክ በክልሉ ዋና ከተማ ዲኒፕሮ አንድ የመኖሪያ ቤት ሙሉ በሙሉ ሲወድም የገበያ ማዕከል ተጎድቷል ሲሉ ተናግረዋል ።

ሌሊቱን በተፈጸመው ጥቃት በሰው ሕይወት ላይ ጉዳት ባይደርስም ሊሳክ እንደተናገሩት ቅዳሜ ከሰአት በኋላ በሩስያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት አራት ሰዎች ቆስለዋል።

ሩሲያ ዲኒፕሮፔትሮቭስክ ዒላማ ያደረገችው ለሁለት ተከታታይ ምሽቶች ጥቃቶችን ከሰነዘረች በኋላ ነው።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ኪየቭ የሩስያ ጦር ወደ ክልሉ መግባቱን እና እግረኛውን ጦር ለማስፈር እየሞከረ መሆኑን ተናግራ ነበር።

በዋና ከተማዋ ኪየቭ አቅራቢያ የባቡር መሠረተ ልማቶች የወደሙ ሲሆን የቅርብ ጊዜዎቹ ጥቃቶች ከፍተኛ ጉዳት ያስከተሉት በማዕከላዊ እና ደቡብ ምሥራቅ ዩክሬን ነው።

በማዕከላዊ ምሥራቃዊ ክልሎች ፍንዳታዎች ከተሰሙ በኋላ የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በዛፖሪዝሂያ ጥቃት የተነሳውን እሳትን ሲያጠፉ ታይተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬን ጦር ሰው አልባ አውሮፕላኖች በሩሲያ ክራስኖዳር እና ሲዝራን ውስጥ የሚገኙ የነዳጅ ማጣሪያ ተቋማትን ደብድበዋል።

ሁለቱም ማጣሪያዎች ከዚህ ቀደም ዒላማ ተደርገው ነበር።

የዩክሬን ጦር በክራስኖዶር በሚገኘው ተቋም በርካታ ፍንዳታዎች እና ቃጠሎዎች ተከስተው እንደነበር ተናግሯል።

እንደ ኪየቭ መረጃ ከሆነ ማጣሪያዎቹ በዓመት ሦስት ሚሊዮን ቶን ነዳጅ ያመርታሉ።

መከላከያው በሲዝራን በሚገኘው ማጣሪያ ላይ የእሳት ቃጠሎ መከሰቱን ገልጾ፣ ይህም በየዓመቱ ከስምንት ሚሊዮን ቶን በላይ ነዳጅ ያመርታል ብሏል።

በክራስኖዶር የሚገኙ የሩሲያ ባለስልጣናት የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች በነዳጅ ማጣሪያው ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተናግረዋል።

ከማጣሪያው ክፍሎች በአንዱ ጉዳት ደርሶ የእሳት ቃጠሎ መከሰቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ተናግረዋል።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በክሬሚያ 18 እንዲሁም ሌሎች የሩሲያ አካባቢዎች ሁለት በአጠቃላይ 20 የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትቶ መጣሉን አስታውቋል።

የሩስያ ጦር ቅዳሜ ማለዳ ላይ በምሥራቃዊ ዶኔትስክ ክልል የሚገኘውን ኮምይሼቫካ የተባለ አካባቢን መያዙን ገልጿል። ዩክሬን ግን ይህንን አላረጋገጠችም።

ከቅርብ ወራት ወዲህ የሩስያ ወታደሮች በዩክሬን ምሥራቃዊ አካባቢ ከፍተኛ መከላከል እየገጠማቸው ቢሆንም ቀስ በቀስ ወደፊት መግፋታቸውን ቀጥለዋል።

የሩሲያ ጦር ዋና አዛዥ ቫለሪ ገራሲሞቭ ቅዳሜ ዕለት እንደተናገሩት ጦሩ "በጠቅላላው የመከላከያ ግንባር ላይ የሚያደርገውን የማያቋርጥ ጥቃት" ቀጥሏል ።

የአርብ ምሽቱ የሁለቱ አገራት የአየር ጥቃት ጦርነቱን ለማስቆም አሜሪካ የምታደርገው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ፍሬ ሳያፈራ መቅረቱን ማሳያ ነው።

ዜሌንስኪ የቅርብ ጊዜ ጥቃቶች ሩስያን "ንግግሮችን ችላ ማለቷን ያሳያል" ብለዋል። ከሩሲያ ጋር ለመነጋገር ብቸኛው መንገድ ማዕቀብ መጣል ነው ሲሉም አሳስበዋል።

"ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ እና ከመላው ዓለም እርምጃ እንጠብቃለን" ሲሉም አክለዋል።

የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዩክሬን ያለውን ጦርነት ጨምሮ ስለ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ለመነጋገር በዚህ ሳምንት መጨረሻ በዴንማርክ ተገናኝተዋል።

ከመወያያ አጀንዳዎቹ ቁልፍ ጉዳዮች አንዱ በግምት ወደ 245 ቢሊዮን ዋጋ ያላቸው የሩሲያ ንብረቶችን እንዳይንቀሳቀሱ ማድረግ ነው።

በስብሰባው ላይ የተገኙት የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ካጃ ካላስ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ቢደርግም "ሩሲያ ሰላም እንደማትፈልግ" ግልጽ ነው ብለዋል።

ፈረንሣይ፤ ስብሰባውን ተጠቅማ በሩሲያ ላይ ማዕቀብ የሚጣልበትን አዲስ ምክረ ሃሳብ ማቅረብ ዓላማው፤ "ሩሲያ በዚህ ጦርነት ላይ የምታፈሰውን ሀብት" ማዳከም እንደሆነ ገልጻለች።