ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት እንደምትደግፍ በድጋሚ አረጋገጠች
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በዩክሬን ጦርነት ላይ ለሞስኮ ያላቸውን "ድጋፍ ያለ ቅድመ ሁኔታ" እንደሰጡ የፒዮንግያንግ መንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
በሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በተደረገ ውይይት ፒዮንግያንግ "የዩክሬን ቀውስ ዋና መንስኤን" ለመቅረፍ "የሩሲያ አመራር በሚወስዳቸው እርምጃዎች በሙሉ" ከጎን መቆሟን ተናግረዋል።
የምዕራባውያን ባለሥልጣናት ፒዮንግያንግ ባለፈው ዓመት ዩክሬንን ለመዋጋት ወደ 11,000 የሚገመቱ ወታደሮችን ወደ ሩሲያ እንደላከች ያምናሉ።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየካቲት 2022 ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ ወርረዋል።
የሰሜን ኮሪያ መንግሥት ብሔራዊ መገናኛ ብዙኃን የሆነው ኬሲኤንኤ የዜና ወኪል እንደዘገበው ኪም እና ላቭሮቭ ቅዳሜ እለት የተገናኙት "በፍቅር ጓዳዊ መተማመን በተሞላበት ድባብ" ነበር።
የሰሜን ኮሪያ መሪ በተጨማሪም "የሩሲያ ጦር እና ሕዝብ የአገሪቱን ክብር እና መሠረታዊ ጥቅሞችን ለማስጠበቅ የተቀደሰ ዓላማን በማሳካት ድል እንደሚያደርጉ ጽኑ እምነት" እንዳላቸው ተናግረዋል።
የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቴሌግራም ገፁ ላይ ሁለቱ ባለሥልጣናት ሲጨባበጡ እና ተቃቅፈው ሰላምታ ሲሰጡ የሚያሳይ ቪዲዮ ለጥፏል።
ላቭሮቭ ከሰሜን ኮሪያው አቻቸው ቾ ሶን ሁይ ጋር ተገናኝተው ሩሲያን ለመርዳት የተሰማሩትን "ጀግና" የሰሜን ኮሪያ ወታደሮችን አመስግነዋል ሲል ታስ (TASS) የሩስያ የዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የሰሜን ኮርያ ለሩሲያ የምታደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ ዳግም ያረጋገጠችው ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የምታደርገውን ወታደራዊ የመሣርያ አቅርቦት ለአጭር ጊዜ ተቋርጦ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም በጀመሩበት ወቅት ነው።
ትራምፕ ባለፈው ሐሙስ ለኤንቢሲ ኒውስ እንደተናገሩት አሜሪካ ለዩክሬን የአየር መቃወሚያ ለመላክ ከሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።
ምዕራባውያኑ ወደ ሩሲያ እና ዩክሬን ጦር ግንባር መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እንቅስቃሴ ካደረጉ ከወራት በኋላ ፒዮንግያንግ ወታደሮቿን ወደ ሩሲያ መላኳን ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ አምናለች።
ኪም ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ከሩሲያ መሪ ቭላድሚር ፑቲን ጋር ሁለቱም አገራት "ጥቃት" የሚፈጸምባቸው ከሆነ እርስ በርስ ለመደጋገፍ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ሰሜን ኮሪያ ከወታደሮቿ በተጨማሪ በጦርነት ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባትን ኩርስክ ግዛት መልሶ ለመገንባት በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞችን ለመላክ ቃል መግባቷን የሞስኮ የጸጥታ ኃላፊ ባለፈው ወር ተናግረዋል።