ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዕቃ የመግዛት ሱስ እንዳለ ያውቃሉ?
አዳዲስ ልብስ፣ ጫማ፣ ቦርሳ ወይም ሽቶዎች መግዛት ደስ የሚል ስሜት ሊፈጥር ይችላል። ነገር ግን አዳዲስ ዕቃዎች ለመግዛት የማይቆጣጠሩት ስሜት ቢሰማዎት እና መግዛት ማቆም ባይችሉስ?
በዕቃ መግዛት ሱስ ከተጠመዱ መካከል ገንዘብ ሳይኖራቸው እንኳን በሺዎች ፓውንዶች ዕዳ ውስጥ ገብተው ዕቃዎችን የሚገዙ እንዳሉ ቢቢሲ ካናገራቸው የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ነዋሪዎች ሰምቷል።
ቁጥር በሌላቸው ሸሚዞች፣ ቀሚሶች፣ ሱሪዎች የተከበበችው ሉሲ ካለችበት ሕይወት እንደ ማምለጫ የምትጠቀመው አዳዲስ ልብሶችን በመፈለግ ሲሆን በቀንም 14 ሰዓትን ያህል በዚሁ ታሳልፋለች።
አዳዲስ ልብሶች በየጊዜው መግዛት ከፍተኛ የሕይወቷ አካል የሆነው የ37 ዓመቷ ኑሮ አስደሳች ሊመስል ይችላል፤ ነገር ግን ለሉሲ ይህ ከመጠን በላይ አላስፈላጊ የሆነው መግዛቷ ሕይወቷን እንዳበላሸው ትናገራለች።
ይባስ ብሎ ልብስ ለመግዛት ስትል መሠረታዊ የሆኑ ክፍያዎችን ሳትከፍል የቀረችበት ወቅት አለ።
"በአካልም ሆነ በመንፈስ እንደዋዠቅኩ ነው። ልብሶቼ ሸክም ነው የሆኑብኝ" ትላለች።
ሉሲ ምን ያህል አልባሳት እንዳላት አታውቅም።
ነገር ግን በዩናይትድ ኪንግደም ምዕራብ ዮርክሻየር መኖሪያ ቤቷ ውስጥ አንድ ሙሉ ክፍል እና በርካታ ሻንጣዎች አልባሳቶቿን የያዙ ናቸው።
እነዚህ ብቻ አይደሉም አንድ መጋዘንም እንዲሁ ልብሶች ተሞልተዋል።
"ልብሶች በእውነተኛ ሕይወቴ እየሆነ ያለውን እንዳይሰማኝ ጋሻ ሆነውኛል" ስትል ትገልጻለች።
ሉሲ በኢንስታግራም የተለያዩ ፋሽኖችን የምታሳይበት ገጽ መክፈቷን ተከትሎ ወጪዋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ።
ከዚያም በሳምንት 700 ፓውንድ ማውጣት ጀመረች። በራሷም መክፈል ስላልቻለች እየተበደረች መግዛት የጀመረችው ሉሲ ዕዳዋ 12 ሺህ ፓውንድ ደረሰ።
"ስነቃ የማስበው የመጀመሪያው ነገር ልብስ ነበር" ትላለች
"ያሉበትን የሕይወት እውነታ ለማምለጥ መጠጥ እንደሚጠጡት እና በመጠጣት እንደሚቀጥሉት ልብስም የምትገዛው በዚያው መንገድ ሙሉ በሙሉ ማምለጫዋን ለማግኘት ነው" ትላለች አሁን ከዚህ የልብስ መግዛት ሱስ እያገገመች ያለችው ሉሲ።
በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በርካታ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ቁጥር አልባ ልብሶች ሲኖራቸው ስታይ የእሷንም ሁኔታ የተለመደ ነው የሚል ስሜት እንዲፈጠርባት አደረጋት።
ችግር እንዳለባት የማታውቀው ሉሲ በአንድ ወቅት ነው አንድ የሥነ ልቦና ባለሙያ (ቴራፒስት) ኦኒዮማኒያ ወይም ዕቃዎችን የመግዛት ከፍተኛ ጉጉት ችግር እንዳለባት የነገሯት።
ሉሲ በዚህ ወቅት ነው ዕቃዎችን መግዛት ሱስ እንደሚሆን ያወቀችው።
የመግዛት ሱስ ወይም ኦኒዮማኒያ በመባል የሚታወቅ እክል ሲሆን፣ ይህም ሰዎች መቆጣጠር በማይችሉበት ሁኔታ የመግዛት ወይም ወጪ የማድረግ ፍላጎት ሲሰማቸው ነው።
ምን ያህል ሰዎች ይህ እክል እንዳለባቸው አይታወቅም።
ነገር ግን አንዳንድ ጥናቶች 5 በመቶ ገደማ የሚሆኑ አዋቂዎች በዚህ ሱስ መጠቃታቸውን የጠቆሙ ሲሆን፣ ነገር ግን በቅርብ ጊዜ የተደረገ ጥናት ደግሞ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ በኋላ አሃዙ ወደ 10 በመቶ ከፍ ማለቱን አሳይቷል።
ሉሲም ሆነ በዩናይትድ ኪንግደም ያሉ ሌሎች ስለ ሁኔታው የተሻለ ግንዛቤ እንዲሁም ከብሔራዊ የጤና አገልግሎት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግላቸው እየጣሩ ነው።
ሆኖም በኦኒዮማንያ ላይ ያለው ምርምርም ሆነ አረዳድ ገና እንደሆነ ነው የምትናገረው።
በሮተርሃም ነዋሪ የሆነችው ናታሊ በበኩሏ በመኖሪያ ቤቷ ውስጥ 10 ሺህ ዕቃዎች ተከማችተው ይገኛሉ።
የ40 ዓመቷ ናታሊ ይህ መቆጣጠር የማትችለው የግዢ ስሜት የተወሰኑ ዓይነት ዕቃዎችን እንዲሁም ቀለሞችን እንድትገዛ ያደርጋታል።
ቁም ሳጥኗ ውስጥ 300 የጥርስ ሳሙና እንዲሁም 3 ሺህ የልብስ ማጠቢያ አነስተኛ ሳሙናዎች ተጠራቅመውበታል።
ሱስዋ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት በየቀኑ መደብሮች እየሄደች ዕቃዎችን ትሸምት ጀመር።
ወጪዋም 3000 ፓውንድ በወር የደረሰ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 1 ሺህ ፓውንድ የሚሆነው ወደ መታጠቢያ ቤት ዕቃዎች ነው የሚሄደው።
"ማቆም አልችልም፤ እኔም ማቆም አልፈልግም። የሆነ ነገር ኦንላይን ላይ ካየሁ እፈልገዋለሁ። እንዴት እንደማገኘው ግድ የለኝም። መግዛት አለብኝ" ትላለች።
የአንድ ልጅ እናት የሆነችው ናታሊ በቅርቡ በአንድ በረራ ላይ እያለች በዋናነት ሽቶ ለመግዛት 1 ሺህ ፓውንድ አውጥታለች። በቤቷም ባለፉት ሁለት ዓመታት ያህል የገዛቻቸው 400 ሽቶዎች አሏት።
በሙያዋ ነርስ የሆነችው ናታሊ ማስታወቂያዎች በምትገዛቸው ዕቃዎች ላይ ከፍተኛ ስፍራ አላቸው ትላለች። ሥራ በሌላትም ወቅት በቀን ስድስት ሰዓት ያህል የሽቶ ቪዲዮዎች እያየች እንደምታሳልፍ ትናገራለች።
በብሔራዊ የጤና አገልግሎት እንዲሁም በግሏ የሥነ ልቦና ባለሙያ አማክራለች፤ ነገር ግን ግዢዋን ለማቆም ዝግጁ ባለመሆኗ እንዳልተሳካ ታስረዳለች።
ሆኖም አሁን በተወሰነ መልኩ ለመቀነስ እየሞከረች ነው።
ቢቢሲ ዕቃ የመግዛት ሱስ አለብን ያሉ 15 ግለሰቦችን አናግሯል።
በርካቶቹ ምን ያህል የአእምሮ ጤናቸውን እንዳቃወሰው ያስረዱ ሲሆን፣ የጥፋተኝነት እና የእፍረት ስሜት ይሰማናል ብለዋል።
ዕቃ የመግዛት ሱስ የአመጋገብ እክል አድርሶብናል፤ በሕይወቴ ውስጥ "ጭራቅ ሆኖብኛል" ያሉም አልታጡም። ሁሉም ቢሆን የሚስማሙበት ነገር ቢኖር ማኅበራዊ ሚዲያዎች ለዚህ ሱሳቸው አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ።
በኦንላይን የሚደረግ የዕቃዎች ሽያጭ ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ በእጥፍ መጨመሩን ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
በአውሮፓውያኑ 2015፣ 12 በመቶ የነበረው አሃዝ በ2025 ወደ 27 በመቶ ጨምሯል።
ይህ ብቻም ሳይሆን የዲጂታል ማስተዋወቂያዎችን በበላይነት የሚያየው አይኤቢ ዩኬ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የአስተዋዋቂዎች ወጪ ከባለፈው ዓመት 20 በመቶ ማደጉን ገልጾ፣ ይህም 8.87 ቢሊዮን ፓውንድ ደርሷል ብሏል።
በመላው ዩናይትድ ኪንግደም የሱስ ሕክምናዎችን የሚሰጠው የዩኬ ኤቲ ቡድን የቴራፒ ዳይሬክተር የሆኑት ዛሂን አህመድ ዕቃ የመግዛት ሱስ ያለባቸው በርካታ ሰዎች ወደ ማዕከሎቻቸው እየመጡ እንደሆነ ያስረዳሉ።
"ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሕይወታችን ላይ ትልቅ ተጽእኖ እያሳደሩ ነው። ለመግዛት፣ ገንዘብ ለማውጣት፣ በእያንዳንዷ ወቅት ከሰዎች ጋር ለመነጋገር ከፍተኛ ጉጉት እያሳደሩብን ነው" ብለዋል።
አሊስ በራስ መተማመኗ እና ለራሷ ያላት ግምት አነስተኛ በመሆኑ ነበር ዕቃ መግዛትን እንደ መውጫ መንገድ ያየችው።
ገና 18 ዓመት ሲሆናትም 'ባይ ናው ፔይ ሌተር' በተሰኘ ዕቅድ በብድር ልብስ መሸመት ጀመረች።
አሊስ ልብሶችን በኦንላይን በማዘዝ የወር ወጪዋ እስከ 800 ፓውንድ ሆኖ መጨረሻ ላይም 9 ሺህ ፓውንድ ዕዳ ተጫነባት።
"አዲስ ዕቃ ስከፍት ከፍተኛ ደስታ ነበረው። ነገር ግን ይህ ስሜት የሚቆየው ለትንሽ ጊዜ ነው። እንደገና ሐዘኔ ይመለሳል። ስለዚህ እንደ አዲስ መግዛት እጀምራለሁ" ትላለች።
በአሁኑ ወቅት የ25 ዓመት ወጣት የሆነችው አሊስ በንግድ አስተዳደር ውስጥ የምትሠራ ሲሆን፣ በሥነ ልቦና ባለሙያ እገዛ ከሱሷ ተፈውሳለች። ከዕዳ ነጻ ለመሆንም ጫፍ ላይ ናት።
"ይሄንን ባላደርግ ኖር አሁን የት እንደምገኝ አላውቅም" ትላለች።
የብሔራዊ ጤና አገልግሎት ሰው በማንኛውም ነገር በሱስ ሊያዝ እንደሚችል የሚገልጽ ቢሆንም፤ የዕቃ መግዛትን ሱስ ለመለየት የሚደረግ የተለየ ምርመራ የለም።
ለዚህም አንደኛው ምክንያት ባለሙያዎች መንስዔዎቹ እንዲሁም መለያዎቹ በሚለው ላይ ስምምነት ስሌላቸው ነው።
አንዳንዶች የባህሪይ ሱስ ነው ብለው ሲያምኑ፣ ሌሎች ደግሞ ከስሜት መዋዠቅ ወይም መቆጣጠር ከማንችላቸው እክሎች ጋር ያይዙታል።
በዮርክ ዩኒቨርስቲ የሱሰኝነት ፕሮፌሰር ኢያን ሃሚልተን፣ ዕቃ የመግዛት ሱስ በአእምሮ ሕክምና ሙያ ዘርፉ "ጭራ ነው" ይላሉ።
በዘርፉ ለሦስት አስርት ዓመታት ያገለገሉት ባለሙያው የመግዛት ሱስ መደበኛ ምርመራ ተደርጎ በእክልነት እስኪለይ ድረስ ገና ሁለት ወይም ሦስት ዓመታትን ሊወስድ ይችላል ይላሉ።
ፕሮፌሰር ሃሚልተን እንደሚሉት የኦንላይን ሻጮች ደንበኞቻቸውን ለማጥመድ ልክ የቁማር ኢንዱስትሪው የሚጠቀሙባችን አንዳንድ ስልቶች ወስደዋል።
"ሰዎች ገንዘብ በማውጣታቸው እና በመግዛታቸው ጥሩ ስሜት ከተሰማቸው በኋላ እንደገና ወደ ጸጸት የመመለስ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸው በአጋጣሚ የመጣ አይደለም" ሲሉ ያስረዳሉ።
ምሁሩ የተጽዕኖ ፈጣሪዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር እንዲሁ በአጋጣሚ የመጣ እንዳልሆነም ነው የሚናገሩት።
ማራኪ በሆኑ ቪዲዮዎች ተቀነባብረው የሚተዋወቁ ምርቶች ያላቸው ተጽዕኖም ከፍተኛ ነው ይላሉ።