ከኢትዮጵያ መሪ ጋር የተገናኙት የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለአገራቸው ድጋፍ ጠየቁ

የዩክሬን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ጨምሮ ከአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ጋር በአዲስ አበባ ውይይት ያደረጉት የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሜትሮ ኩሌባ አፍሪካ ለአገራቸው ድጋፍ እንድትሰጥ ጠየቁ።

ለሁለተኛ ጊዜ የአፍሪካ ጉብኝታቸውን እያደረጉ ያሉት የዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ረቡዕ ግንቦት 16/ 2015 ዓ.ም አዲስ አበባን ጎብኝተዋል።

ሚኒስትሩ የአፍሪካ አገራት በሩሲያ ወረራ ላይ ገለልተኛ አቋም ከማንጸባረቅ እንዲቆጠቡም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

“ሩሲያ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ወረራ ገለልተኛ አቋም ማንጸባረቅ ማለት፣ ድንበር መጣስን፣ መጠነ ሰፊ ወንጀሎችን መፈጸም ላይ ገለልተኛነትን እንደማሳየት ነው” በማለት አዲስ አበባ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

ባለፈው የካቲት የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ሩሲያ ከዩክሬን ግዛት እንድትወጣ በሚጠይቀው ዉሳኔ ላይ ድምጽ በሰጠበት ወቅት ከ54 የአፍሪካ አገራት ብዙዎቹ ተአቅቦ ወይም ድምጽ ባለመስጠት ነበር አቋም የወሰዱት።

ኤርትራና ማሊ በበኩላቸው ውሳኔውን በመቃወም ለሩሲያ ድጋፋቸውን በይፋ የሰጡ አገራት ነበሩ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አገራቸው ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላትን ግንኙነት በውጭ ፖሊሲዋ ላይ ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቷ ኪሳራዎችን ማስተናገዷንም አምነዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀ መንበርና የኮሞሮስ ፕሬዚዳንት አዛሊ አሱማኒ ጋር ተወያይተዋል።

ከዓመት በላይ በዘለቀው ጦርነት ምክንያት የአፍሪካ የእህል እና ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተከትሎ በደቡብ አፍሪካ የሚመራ የስድስት አፍሪካ አገራት የሰላም ተነሳሽነት ተጀምሯል። ይህ ጅማሮ በዩክሬንና ሩሲያ ያለውን ጦርነትም ለመቋጨት ያቀደ ነው።

ከዚህ ቀደም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጠራቸው ውይይቶች ላይ ምዕራባውያን አገራት የሩሲያን ወረራ ሲያወግዙ ቢሰሙም የአፍሪካ አገራት ድምጸ ተዓቅቦ በማደረጋቸው ለምዕራባውያን ትችት አጋልጧቸዋል።

ኤርትራ እና ማሊ በበኩላቸው የተባበሩት መንግሥታት አቋም ተቃውመው ድምጻቸውን ሰጥተዋል።

የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን የጎበኙ የመጀመርያው የዩክሬን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሜትሮ ኩሌባ ሞሮኮን እና ሩዋንዳን በቀጣይነት ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሚኒስትሩ ለመጀመርያ ጊዜ አፍሪካን የጎበኙት በፈረንጆቹ ጥቅምት ወር ላይ ሲሆን በዚህ ጉብኝታቸውም ሴኔጋል፣ አይቮሪ ኮስት፣ ጋና እና ኬንያን ጎብኝተዋል።