ሂዩማን ራይትስ ዎች በምዕራብ ኦሮሚያ ሰላማዊ ዜጎች ጥበቃ አላገኙም አለ

ሂዩማን ራይትስ ዎች ባለፈው ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. በምዕራብ ኦሮሚያ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች በታጣቂዎች ሲገደሉ የኢትየጵያ መንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ጥቃቱን ለመከላከል በቂ ጥበቃ አላደረጉም ነበር አለ።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቅዳሜ ሰኔ 11/2014 ዓ.ም. በኃይል የታጠቁ ኃይሎች ስምንት ሰዓታት በፈጀ ጥቃት ሴቶች እና ህጻናትን ጨምሮ 400 የሚጠጉ ሰላማዊ የአማራ ተወላጆችን ቶሌ እና ሰኔ ቀበሌዎች ውስጥ ገድለዋል ብሏል።
ማንነታቸው ያልታወቁ ያላቸው ታጣቂዎች ከጥቃቱ ባሻገር በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን ከማቃጠል ባለፈ ዝርፊያም ፈጽመዋል ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች።
ከሳተላይት በተገኘ መረጃ መሠረት በአምስት የገጠር አካባቢዎች ቃጠሎ መድረሱን እና 480 የሚጠጉ ግንባታዎች መወደማቸውን በመግለጫው ጠቅሷል።
"የመንግሥት ኃይሎች ምንም አላደረጉም"
የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር “የታጠቁ ኃይሎች መንደሮችን አንድ በአንድ አወድመዋል፤ መላ ቤተሰብን በጭካኔ ገድለዋል፤ ይህ ሁሉ ሲሆን በአቅራቢያው ያሉ የመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች ምንም አላደረጉም" ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ በጥቃቱ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ተዓማኒ እና ገለልተኛ ምርመራዎችን ማከናወን፣ ተጠያቂ የሆኑትን መለየት እና ጉዳት ለደረሰባቸው በቂ እርዳታ ማድረስ አለበት ብለዋል።
የመንግሥት ኃይሎች እና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ባለፉት ዓመታት በምዕራብ ኦሮሚያ ሲዋጉ ቆይተዋል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ በአካባቢው ቀጥሎ የተካሄደው ጦርነት ለኦሮሞዎች እና በአካባቢው ለሚኖሩ አናሳ ቁጥር ላላቸው ሌሎች ብሔሮች ከፍተኛ እንግልት ምክንያት ሆኗል ብሏል።
ሰኔ 2014 ዓ.ም. ለደረሰው ጥቃት ሁለቱም ወገኖች አንዳቸው ሌላኛውን ተጠያቂ አድርገዋል።
". . . ‘ጨርሷቸው። እንዳትለቋቸው'. . ."
ሂዩማን ራይትስ ዎች በአካባቢው የሚገኙ 37 ሰዎችን በስልክ አነጋግሯል። የሟቾችን ማንነት ከነዋሪዎች ያገኘ ሲሆን ከጥቃቱ በፊት እና በኋላ ያሉ የሳተላይት ምስሎችንም አጢኗል።
በሥራ ላይ የነበረ አንድ አርሶ አደር በመኖሪያ አካባቢው ጪስ በማየቱ እና የተኩስ ድምጽ በመስማቱ ወደ ቀዬው ሲመለስ አካባቢው በታጣቂዎች መከበቡን አስታውቋል።
“ልጆቼን ይዤ ወደ ጫካ በመግባት ተደበቅኩኝ። ታጣቂዎቹ በኃይል የታጠቁ ናቸው። ‘ጨርሷቸው። እንዳትለቋቸው። ጨርሷቸው’ ሲሉ ሰማሁኝ” ብሏል።
ከጨቆርሳ ከልጇ ጋር ወደ በቆሎ ማሳ የሸሸች እናት ተደብቀው ባሉበት የስምንት ወር ልጇ ማልቀስ መጀመሩን ታስታውሳለች።
“ልጁ ሲያለቅስ አንዱ ወደ እኛ አቅጣጫ እየጠቆመ ‘እዛ ተመልከት’ አለ። ልጄን ተኩሰው ገደሉት። በለበስኩት ልብስ አስክሬኑን ሸፈንኩት። ሌላኛዋ ልጄ ጀርባዋ ላይ ተመታ ጥይቱ በአንገቷ ወጣ። ልጄን ወደ ደረቴ አቅፌ አላህ እንዲጠብቃት መጸለይ ጀመርኩ” ስትል የነበረውን ገልጻለች።
በትንሹ በስድስት መንደሮች ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ሟቾችን የቀበሩ ነዋሪዎች መናገራቸውንም ገልጿል።
የማህበረሰቡ መሪ በሲልሳው 112፣ በጨቆርሳ 105፣ በጉትን 37፣ በቤጊ 72፣ በሃያዋ 16 እና በሰኔ ቀበሌ ደግሞ 16 መገደላቸውን ጠቁመዋል ብሏል ሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ቡድን።
እስከ ሰኔ 23 በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የ338 ሰዎች ማንነት መለየቱን አስታውቆ ነበር።
ተመሳሳይ ጥቃቶች በቄለም ወለጋ እና ምዕራብ ወለጋ ተፈጽመው ከፍተኛ ቁጥር ያለቸው ሰዎች መገደላቸውን መገናኛ ብዙሃን መዘገባቸውን አስታውሷል።
ተፈናቃዮች እና የሰብዓዊ እርዳታ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (ኦቻ) ከቶሌ ብቻ 4800 ሰዎች መፈናቀላቸውን ገልጿል። ከምዕራብ ኦሮሚያ ደግሞ 500 ሺህ ሰዎች ተፈናቅለዋል ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው አፋጣኝ እርምጃ በታጣቂዎች ላይ “የሕግ ማስከበር እርምጃውን አጠናክሮ መቀጠል” ነበር ብሏል ድርጅቱ።
የአገሪቱ ፓርላማም ኦሮሚያን ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች በሲቪሎች ላይ የደረሰውን ጥቃት የሚመረምር ልዩ ኮሚቴ እንዲቋቋም ወስኗል።
የቶሌ፣ ሰኔ እና ቦኔ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ግን በምርመራ ረገድ ያዩት ነገር ኢሚንት መሆኑን ጠቁመዋል ብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊ ሚሼል ባቼል እና የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ በምዕራብ ኦሮሚያ ገለልተኛ ምርመራ እንዲከናወን ጠይቀዋል።
"በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ ማህበረሰቦች በተደጋጋሚ በሚደርስባቸው ጥቃቶች በስጋት ቆይተዋል። አሁንም ቀጣዩን ጥቃት በመፍራት በስጋት እየኖሩ ነው" ያሉት ሌቲሻ ባድር "የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እርምጃ ለመውሰድ እና ለተጎዱ ማህበረሰቦች አስቸኳይ እና በቂ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ በመስጠት እና ለገለልተኛ ምርመራዎች ድጋፍ ለመስጠት የገቡት ቃልን በመወጣት በአስቸኳይ መንቀሳቀስ አለባቸው" ብለዋል።
መንግሥት እና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ሰብዓዊ ድጋፍ ማደረጋቸውን ቢገልጹም ነዋሪዎች ከአንድ ጊዜ በላይ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው ተናግረዋል ብሏል።
ሂዩማን ራይተስ ዎቸ መንግሥት ምርመራ በማድረግ እና የደረሰውን ጉዳት በመለየት ረገድ ያደረገውን እንቅስቃሴ እንዲያሳውቅ ጠይቋል።
ለተጎጂዎች አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ፣ በጥቃቱ እጃቸው ያሉበት የሥራ ኃላፊዎች ሚና እንዲመረመር፤ በጸጥታ ኃይሎች ላይም ነጻ እና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቋል።
በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ የኦሮሞ ነጻነት ጦር እና ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች በሲቪሎች እና በንብረታቸው ላይ የሚያደርሱትን ሕገ ወጥ ጥቃት በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጠይቋል።
በሕገ ወጥ ጥቃቶች የተሳተፉ አባሎቻቸውንም እንዲቀጡ ጠይቋል።












