ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በመላው ዓለም የወንድ መሃንነት ለምን በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ?
ወንዶችን ለመሃንነት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል አንዱ በመላው ዓለም በሚገኙ ወንዶች ዘንድ የወንድ ዘር ፈሳሽ ውስጥ የዘር መጠን መቀነስ (low sperm count) አንዱ ነው።
ባለፉት ዓመታት መሃን የሚሆኑ ወንዶች ቁጥር ቢጨምር ስለጉዳዩ ብዙ እየተባለ አይደለም።
ተመራማሪዎች አሁን ላይ ለወንዶች የዘረ ፈሳሽ ቁጥር መቀነስ ምክንያቶች ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ የለዩ ይመስላል።
ሁለት ጥንዶች ልጅ ለመውለድ ለሁለት ዓመታት ቢሞክርሙ ወልዶ ለመሳም አልታደሉም። ስለዚህም የሐኪም ምክር ፍለጋ ያቀናሉ።
“ልንረዳሽ እንችላለን። ከባድ አይደለም። እንረዳሻለን” በማለት ዶክተሩ ለጄኔፈር ሃኒቲንግተን ይነገራታል። ከዚያም ሐኪሙ ፊቱን ወደ ጄኔፌር ባለቤት ሲአራና አዞረና፤ “አንተን ግን መርዳት አንችልም” አለው።
ከዮርክሻየር እንግሊዝ የሆኑት ጥንዶቹ ቀድሞም ቢሆን ልጅ ለማግኘት የሚያረጉት ጥረት ቀላል እንደማይሆን ያውቁ ነበር። ችግሩ ግን በጄኔፈር በኩል እንጂ በሲአራና በኩል መሆኑን አልጠረጠሩም።
ጄኔፈር ፖሊሳይቲክ ኦቫሪያን ሲንደረም የሚባል እክል አለባት። ይህ ሁኔታ የወር አበባ በተዛባት ሁኔታ ወይም በጣም እየዘገየ እንዲመጣ የሚያደርግ ሲሆን፣ እርግዛና እንዳይፈጠር አሉታዊ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል።
ጥንዶቹ ወደ ሐኪም ጋር ሄደው ያደረጉት ምርመራ ውጤት የሲአራና የዘረ ፈሳሽ ቁጥር አነስተኛ ከመሆኑም በላይ፣ የወንዴ ዘር ፈሳሽ የመንቀሳቀስ ችግር እንዳለበት አሳይቷል። ሲአራና ያጋጠመው ከጄኔፈር በላይ ለማከም አስቸጋሪ ከመሆኑ በላይ ፈጽሞ የማይቻል ነው።
ሁሌም የልጅ አባት የመሆን ጽኑ ፍላጎት የነበረው ሲአራና የምርመራ ውጤቱን ከሐኪሙ ሲሰማ የተሰማውን ሲያስታውስ እንዲህ ይላል። “ድንጋጤ። ሐዘን። በጭረሻ መቀበል አልፈለኩም። ሐኪሙ የተሳሳተ ነበር የመሰለኝ። ...ሕይወቴ ከቁጥጥር ውጪ የወጣ መሰለኝ” በማለት ይናገራል።
ተከትሎ በመጡት ዓመታት የሲአራና የአእምሮ ጤና መታወክ ጀመረ። ብዙ ጊዜ ብቻውን ማሳለፍ እና ከድብርት ስሜት ለመውጣት አልኮልን እንደ አማራጭ መጠቀም ጀመረ።
ወንድ እና ሴቶች በእኩል ደረጃ ለማሃንነት ይጋለጣሉ። በዓለማችን ካሉ ወንዶች ሰባት በመቶ የሚሆኑት በመሃንነት ምክንያት ይብሰለሰላሉ።
ይሁን እንጂ ስለመሃንነት ብዙ አይባልም። አልፎም በማኅበራዊ ምክንያት ስለ ሴቶች እንጂ ስለ ወንዶች መሃንነት ብዙ ሲባል አይሰማም።
ብዙዎችን ወንዶች ለመሃንነት የሚዳርገው ችግር ቀጥተኛ መንስዔ ምንነት በትክክል ማብራሪያ ባይገኝለትም፣ ችግሩ ግን እየሰፋ ስለመሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ።
አንዳንድ ጥናቶች እንደሚሉት ግን የአየር ብክለት የወንዶችን የዘር ፍሬ ጤንነት እየተገዳደረው ነው። ጥናቶቹ ለወንድ የዘረ ፍሳሽ ጥራት መቀነስ ምክንያቱ የአየር ብክለት ነው ብለዋል።
የተደበቀ የመራባት ቀውስ?
ባለፈው ምዕተ ዓመት የዓለም ሕዝብ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። የዛሬ 70 ዓመት ገደማ በዚህች ምድር ላይ 2.5 ቢሊዮን ሕዝብ ብቻ ነበረ። በ2022 የዓለም ሕዝብ በበርካታ ዕጥፍ ተባዝቶ ከ8 ቢሊዮን ተሻግሯል።
ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት በማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች የውልደት መጠን መቀነስን እያሳየ ነው።
ሴቶች የፋይናንስ ነጻነት ማግኘታቸው እንዲሁም በሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ ውሳኔ መስጠት መቻላቸው የውልደት መጠን እንዲቀንስ ምክንያት ነው።
በሌላ በኩል የመዋለድ አቅም እየቀነሰ በመምጣቱ የውልደት መጠኑ እንዲቀነስ ምክንያት ሆኗል። ተመራማሪዎች እንደሚሉት በተለይ ከወንዶች ጋር በተያያዘ እያጋጠሙ ያሉ የሥነ ተዋልዶ ጤና ችግሮች እየጨመሩ ናቸው።
የወንድ የዘር ፈሳሽ ቁጥር መቀነስ፣ የቴስቴስትሮን መጠን መቀነስ፣ የብልት አለመታዘዝ እና የዘር ፍሬ ካንሰር የሚያጋጥማቸው ወንዶች ቁጥር ጨምሯል።
ዋናተኞቹ ሕዋሳት
የማህጸን እና የሥነ ተዋልዶ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሳራህ ማርቲንስ ዳ ሲልቫ የወንድ የዘር ፈሳሽ እጅግ አስደናቂ ሕዋሳት ናቸው ይላሉ።
“በጣም ትንሽዬ ቢሆኑም መዋኘት ይችላሉ። ከሰውነት ውጭ በሕይወት መቆየት ይችላሉ። ይህን ማድረግ የሚችል ሌላ ሕዋስ የለም።”
ይሁን እንጂ እንዲህ አስደናቂ ፍጥረት በሆኑት ሕዋሳት ላይ ትንሽ ለውጥ ከመጣ፣ ከሴት እንቁላል ጋር ተገናኝተው ሕይወት መፍጠር ይሳናቸዋል ይላሉ።
የወንድ የዘር ፈሳሽ ሕዋሳት ከሴቷ እንቁላል ጋር ተገናኝተው ጽንስ የመፈጠሩ ዕድል የሚለካው ምን ያክል የመንቀሳቀስ አቅም አላቸው፣ ቅርጻቸው እና መጠናቸው እንዲሁም በአንድ የዘር ፍሳሽ ውስጥ ምን ያክል ብዛት አላቸው የሚለው ነው።
ባለሙያዎች አንድ ወንድ የመሃንነት ምርመራ ቢያደርግ ምልከታ የሚደረገው ከላይ በተጠቀሱት ዋነኛ ሦስት ጉዳዮች ላይ መሆኑን ይገልጻሉ።
“በአጠቃላይ በአንድ ሚሊሊትር የዘረ ፈሳሽ ውስጥ ከ40 ሚሊዮን በታች የወንድ ዘር ፈሳሽ (ስፐርም) ከተገኘ፤ ስለ የተዋልዶ ጤና ችግር ማሰብ ይጀመራል” የሚሉት በሂብሩ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ጄሩሳሌም ተመራማሪ የሆኑት ሃይ ሌቪን ናቸው።
ምንም እንኳ ከፍተኛ የወንድ ዘረ ፈሳሽ ቁጥር የእርግዝና መፈጠር ዕድልን ይጨምራል ማለት ባይቻልም፤ በአንድ ሚሊሊትር ውስጥ የሚገኘው የዘር ፈሳሽ ከ40 ሚሊዮን በታች ከሆነ እርግዝና የመፍጠር አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ይወርዳል ይላሉ።
ሌቪን እና ተባባሪ ተመራማሪዎች ባካሄዷቸው ጥናቶች ከአውሮፓውያኑ 1973 እስከ 2018 በዘር ፈሳሽ ውስጥ ያለው መራባት የሚችለው የዘረ ፈሳሽ መጠን በየዓመቱ በ1.2 በመቶ መቀነሱን አረጋግጠዋል።
ለዘረ ፈሳሽ ቁጥር መቀነስ ምክንያቶች ደግሞ በሰዎች ዘረመል ላይ ለውጥ መምጣት፣ የአኗኗር ዘዬ እና የከባቢ ሁኔታ መቀያየር ተጠቃሽ ናቸው።
“የልጅ አባት የመሆን ፍላጎት አለመሳካት፤ የማርገዝ ሕልም እውን አለመሆን እጅግ ስሜት የሚሰብር ቢሆንም፤ የዘረ ፈሳሽ ቁጥር የቀነሰበት መጠን በማኅበረሰብ ደረጃ የከፋ ችግር ውስጥ እንዳለን ነው የሚያሳየው” ይላሉ ዳ ሲልቫ።
በዩናይትድ ኪንግደም ኖቲንግሃም ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ የሆኑት ሬቤካ ብላንካርድ በአካባቢያችን ያሉ ቁሶች እና የአየር ብክለት በወንዶች የሥነ ተዋልዶ ጤና ላይ የሚያመጡትን ችግር ሲያጠኑ ቆይተዋል።
ጥናታቸው በሰዎች መኖሪያ ቤቶች ውስጥ በሚገኙ ፕላስቲኮች እና በተለመዱ የቤት ውስጥ እቃዎች ውስጥ የተከማቹ ኬሚካሎች የሰዎችን የሆርሞን ሥርዓት እንደሚያውኩ እና የመሃንነት ችግር ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አሳይተዋል።
ሱስ እና የአኗኗር ዘይቤ
ከከባቢያዊ ሁኔታዎች በተጨማሪ የግለሰቦች የአኗኗር ዘይቤ ለመሃንነት ሊያጋልጡ ይችላሉ።
ጤናማ ያልሆነ የአመጋገብ ሥርዓት፣ አካላዊ እንቅስቀሴ አለማድረግ፣ ጭንቀት፣ የአልኮል መጠጥ እና አደንዛዥ ዕጽ መጠቀም ችግሩን የሚያባብሱ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ስለ ወንድ መሃንነት የበለጠ ግንዛቤ እንዲፈጠር፣ ችግሩን ለመከለከል እና የተሻለ ሕክምና ለመስጠት እንዲቻል እንዲሁም ብክለት ለወንዶች መሃንነት ችግር እንዳይሆን ድምጾች እየተሰሙ ነው።
መውለድ አትችልም ሲባል ልቡ ተሰብሮ የነበረው ሲአራና፤ “ብቻህን አትብሰልሰል” ይላል።
ለአምስት ዓመታት በሐኪሞች የቅርብ ክትትል ስር የተለያዩ አይነት የህክም እና ልጅ ለማግኘት የሚያስችሉ አማራጮችን ሲሞክሩ ጥንዶች አሁን ላይ የሁለት ልጆች ወላጆች መሆን ችለዋል።