ኤርትራ ውስጥ የአንድ ታዳጊ ግድያን የተቃወሙ የአንድ መንደር ነዋሪዎች በሙሉ ታሰሩ

ሟች ያፌት የማነ

የፎቶው ባለመብት, Azarya

የምስሉ መግለጫ, ሟች ያፌት የማነ

በኤርትራ ጋሽ ባርካ ክልል በሚገኘው ሎጎ አንሴበ ቀራና ኩዶ መንደር ያፌት የማነ የተባለ ታዳጊ ግድያን ተከትሎ ተቃውሞ ያሰሙ የመንደሩ ነዋሪዎች በአጠቃላይ መታሰራቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተሰብ አባላት ተናገሩ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ከአገር ውጭ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች እና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ነዋሪዎች ግድያው የተፈጸመው ኅዳር 6/2018 ዓ.ም. መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚያ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች ግድያውን በሚመለከት ቅሬታ በማሰማታቸው የሟች ወንድምን ጨምሮ ከ80 በላይ የመንደሩ ነዋሪዎች በመንግሥት ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቤተሰብ አባላት ተናግረዋል።

የ16 ዓመቱ ያፌት በጥይት ከተገደለ በኋላ የአካባቢው ነዋሪዎች ሐሽፌራይ ወደ ሚባል ወታደራዊ ካምፕ ተወስደው መታሰራቸውን የቤተሰብ አባላቱ እና የመንደሩ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።

ሟች ያፌት እና ጓደኞቹ በአካባቢው ከሰል በማክሰል እና በመሸጥ ገቢ ያገኙ እንደነበር የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪ፣ ግድያው ከመፈጸሙ በፊት ከሰል ለመሸጥ ወደ ሕምበርቲ ሲሄድ ከተያዘ በኋላ በወታደሮች እንደተገደለ ተገልጿል።

የያፌት አባት የማነ ገብረማርያም በእስር ላይ በመሆናቸው ልጃቸው ቤተሰቡን እና ራሱን ለመደገፍ ዛፍ ቆርጦ ከሰል ማክሰል ላይ ተሰማርቷል።

በፈረንሳይ የሚኖረው እና የአካባቢው ተወላጅ የሆነው አዛሪያ ለቢቢሲ ትግርኛ እንደተናገረው "ያፌት ቤተሰቡን እና ራሱን ለመደገፍ የሚሠራ ጠንከራ ወጣት ነበር። የአካባቢው ወጣቶች ብዙ ጊዜ ከሰል የሚያከስሉት ሌሊት ነው። ኅዳር 6/2018 ዓ.ም. ያፌት እና ጓደኞቹ ከሕምብርቲ ወደ ቤታቸው ሲሄዱ ወታደሮች በቁጥጥር ሥር አውለዋቸዋል።"

ወታደሮቹ ያፌት እና ጓደኞቹን ከእነ አህዮቻቸው በቁጥጥር ሥር እንዳዋሏቸው የሚናገሩት አቶ አዛሪያ፣ ወደ ካራና ኩዶ መንደር ለመመለስ ሲሞክሩ ወጣቶቹ በማምለጥ በመንደሩ አቅራቢያ ተደብቀዋል ይላሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኋላም ወጣቶቹ አህዮቹን ከወታደሮቹ ለመውሰድ ሞክረው አብዛኞቹ ሲሳካለቸው ሟቹ ያፌት እና ሦስት ጓደኞቹ ግን ሳይሳካላቸው መቅረቱን አቶ አዛሪያ ተናግረዋል።

የያፌት ጓደኞች ወደ ቤታቸው ሲሄዱ እሱ ግን ወደ አህዮች ማቆያ ስፍራ በማምራት ለመውሰድ ሲሞክር ከማን እንደተተኮሰ ባልታወቀ ጥይት ተመትቶ መሞቱን አዛሪያ እና ሌሎች ለቢቢሲ ስለሁኔታው የተናገሩ ሰዎች አስረድተዋል።

እንደ አዛሪያ ገለጻ ከሆነ የያፌት አስከሬን በማግስቱ እኩለ ቀን ድረስ አልተነሳም ነበር። የመንደሩ ነዋሪዎች ሁኔታውን ለባለሥልጣናት ካሳወቁ በኋላም ቁጣ ተቀስቅሷል።

ከዚያ በኋላ ወታደሮች መጥተው አካባቢውን ከበቡ የሚሉት አቶ አዛሪያ፣ ፖሊሶች መጥተው አስከሬኑን ለመመርመር እና ፎቶግራፍ ለማንሳት ሲሞክሩ ተከላክለዋል።

ያፌትም ምንም ዓይነት ምርመራ ሳይደረግለት መቀበሩን አቶ አዛሪያ ጨምረው ተናግረዋል።

የመንደሩ ነዋሪዎች የወጣቱን አሟሟት ስላልተቀበሉ ቅሬታ ማሰማት መጀመራቸውን የሚናገሩት አቶ አዛሪያ ቅሬታቸውን በተለያየ መልኩ ሲገልጹ ወታደሮች ሰብስበው እንዳሰሯቸው ገልጸዋል።

"ግድያው በተፈጸመበት ሳምንት እሁድ ዕለት አብዛኛው ሰው ቤተክርስቲያን ውስጥ በተሰበሰበበት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት ጀምሮ ያሉ ሰዎችን፣ ዲያቆናት፣ የቤተክርስቲያኑን ተማሪዎች እና ካህናት በመንደሩ ውስጥ ያሉትን ከወጣት እስከ አዛውንት ሁሉ ሰብስበው አስረዋል።"

"አሁን በሐፌሽፌራይ ውስጥ እንዳሉ ይነገራል፤ ነገር ግን ምንም የተረጋገጠ ነገር የለም" ሲሉ አቶ አዛሪያ ተናግረዋል።

"ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 80 የሚደርስ ወንዶችን ወስደዋል፤ ከመካከላቸውም የተለያየ ጤና ችግር ያለባቸው እንዳሉ ይታወቃል። የሟች ታላቅ ወንድም ሔኖክ የማነ የሚባል የአእምሮ ጤና መታወክ ያለበት ሳይቀር ነው ተወስዶ የታሰረው።"

በኤርትራ የገጠር አካባቢዎች የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት ስለሌለ ሰዎች ለማገዶ እና ለገቢ ምንጭነት ከሰል በማክሰል ይጠቀማሉ።

የኤርትራ መንግሥት ግን የደን ጠባቂ ወታደሮችን (ፍሩስታለ) በማሰማራት እና የተለያዩ የፍተሻ ጣቢያዎችን በማቋቋም የዛፎች መቆረጥን እና ከሰል ማክሰልን ለመከላከል ይሞክራል።

አዛሪያ በአጠቃላይ የታሰሩ ሰዎች 80 ያህል አንደሚሆኑ ጠቅሶ እስሩ አሁንም በመቀጠሉ ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ያለውን ስጋት ገልጿል።

"ለምሳሌ በረከት የሚባል ቄስ በዚያን ዕለት ሌሎቹ ቁጥጥር ስር በዋሉበት ዕለት ቅዳሴ ላይ ስለነበር በኋላ ላይ ተይዞ ታስሯል። ሌሎችም በተመሳሳይ ከያሉበት እየተፈለጉ ታስረዋል።"

የቀራና ኩዶ አካባቢ ነዋሪዎች ኑሯቸውን የሚገፉት እርሻ በማረስ እና ከብት በማርባት ነው።

የአካበባቢው ነዋሪዎች ከብቶቻቸውን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ራቅ ባለ ስፍራ በአንድ በረት ውስጥ የማኖር ባሕል አላቸው።

የኤርትራ መንግሥት ግን የከብቶቹን በረት በማፍረስ ነዋሪዎች በአንድ መንደር እንዲሰባሰቡ የማድረግ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች እነዚህ የከብት በረቶች "መቃጠላቸውን" የሚገልጹ ዘገባዎች የተሠራጩ ሲሆን፣ አዛሪያ "አንዳንዶቹ በመንደሩ ውስጥ ቤት እንኳን የላቸውም። በሕይወታቸው ሙሉ በበረቶቹ ውስጥ ነው የሚኖሩት ማለት ይቻላል ነው። ነገር ግን መንግሥት በረቶቹን አፍርሰው ወደ መንደሩ ማዕከል እንዲገቡ ነገራቸዋል" ይላል።

የኤርትራ መንግሥት በአንድ አካባቢ ለሚነሳ ተቃውሞ አጠቃላይ የአንድ መንደር ነዋሪዎችን ሲያስር ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ኑሯቸውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረጉት አቶ ደሳለኝ የተባሉ ኤርትራዊ መንግሥት በተለያዩ ጊዜያት ከመሬት ጋር በተያያዙ ለተነሱ ጥያቄዎች የመንደር ነዋሪዎች በሙሉ በጅምላ ማሰሩን የተለያዩ ማስረጃዎችን በመጥቀስ ያስረዳሉ።

ቢቢሲ በጋሽ በርካ ስለተፈጸመው ግድያ እና እስር የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትርን ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።