በኤርትራ ለ24 ዓመታት በእስር ላይ የሚገኘው ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ በሕይወት መኖሩ ተገለፀ

የፎቶው ባለመብት, The Edelstam Foundation
በኤርትራ ለ24 ዓመታት ያለምንም ፍርድ የታሰረው ኤርትራዊው ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ በሕይወት እንዳለ የስዊዲን መንግሥት አርብ ዕለት አስታወቀ።
የስዊድንና ኤርትራዊ ዜግነት ያለው ጋዜጠኛ ዳዊት በሕይወት መኖሩ የተሰማው የስዊድን መንግሥት ከ30 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኤርትራ በመሄድ ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ መሆኑን ኤኤፍፒ ዘግቧል።
የ61 ዓመቱ ጎልማሳ ዳዊት ይስሃቅ እአአ በ2001 ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ የሚጠይቅ ጽሑፍ በጋዜጣ ላይ ካወጣ በኋላ ነበር በኤርትራ መንግሥት በቁጥጥር ሥር የዋለው።
የኤርትራ መንግሥት ወደ 20 የሚጠጉ ከፍተኛ ሚኒስትሮችን፣ የፓርላማ አባላትን እና ነጻ ጋዜጠኞችን ሲያስር ዳዊትም ከእነዚህ መካከል አንዱ ነበር።
ጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ በእስር ላይ በቆየበት ዓመታት አንድም ክስ ያልተመሰረተበት ሲሆን ቤተሰብም ሆነ የትኛውም አካል ስላለበት ሁኔታ መረጃ ለማግኘት ሳይቻል ቆይቷል።
አሥመራ ጋዜጠኛው በእስር ላይ ባለባቸው ዓመታት ሁሉ የት እንዳለ ወይም ስለጤንነቱ ምንም ዓይነት መረጃ ሰጥታ አታውቅም።

የፎቶው ባለመብት, MOI Eritrea
"የእኛ ግምገማ [ጋዜጠኛው] በሕይወት እንዳለ ነው፤ በጉብኝታችን ወቅት ከዚያ ግምገማ ጋር የሚቃረን ምንም አዲስ መረጃ አልደረሰንም" ሲሉ ሚኒስትሯ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የዜና ወኪሉ ስቴነርጋርድ ግምገማቸው የተመሠረተበትን መረጃ ምን እንደሆነ ቢጠይቅም ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
"የእርሱ ከእስር መፈታትና ከቤተሰቡ ጋር መገናኘት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ አድርጌያለሁ" ሲሉ አክለዋል።
የጋዜጠኛ ዳዊት ልጆች የሆኑት ቤተልሄም እና ዳናይት አርብ ዕለት በሰጡት መግለጫ፣ የስቴነርጋርድን ጉብኝት ተከትሎ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
"የስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጉብኝቱ ጋር በተያያዘ አባታችን በቅርቡ እንደሚፈታ ማረጋገጫ እንደተቀበለ እንገምታለን" ብለዋል።
"በተመሳሳይ ጊዜ አሳሳቢ ጥያቄዎች አሁንም አሉ። ኤርትራ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አባታችንን በሰብዓዊነት እንድትለቅ በመስከረም 25 ላቀረበው ጥያቄ እስካሁን ምላሽ አልሰጠችም።"
በተጨማሪም ስዊድን ጋዜጠኛው "በሕይወት ስለመኖሩ በማያሻማ መልኩ የሚያረጋግጥ መረጃ" ማግኘት አለመቻሏ "ትልቅ ሐዘን " እንደሆነ ተናግረዋል።
ስቴነርጋርድ ለኤኤፍፒ እንደተናገሩት የጋዜጠኛ ዳዊት ጉዳይ "ከባድ" ነበር።
"ያለ ምንም ክስ፣ ያለምንም የቆንስላ ግንኙነት ለ24 ዓመታት ታስሯል" ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
ስዊድን ኤርትራ ነጻ አገር መሆኗን ከተቀበለች እአአ ከ1993 ወዲህ አንድ ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣን አገሪቱን ሲጎበኝ ይህ የመጀመሪያው ነው።
የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጋዜጠኛ ዳዊት የሕሊና እስረኛ አድርጎ ይቆጥረዋል።
ዳዊት ወደ ስዊድን የተሰደደው እአአ በ1987ቱ የኤርትራ ጦርነት ወቅት ሲሆን፣ ኤርትራ ነጻ አገርነቷን ካወጀች በኋላ የስዊድን ዜግነት አግኝቶ በ1993 ወደ ትውልድ አገሩ ተመልሷል።
የስዊድንና ኤርትራዊ ዜግነት ያለው ዳዊት በአውሮፓውያኑ 1990ዎቹ በአገሪቱ ውስጥ ከመጀመሪያዎቹ ነፃ ጋዜጦች ውስጥ አንዷ የሆነችውን 'ሰቲት'ን አቋቋመ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የኤርትራ መንግሥት የግል ጋዜጦችን በመዝጋት የሚቀርቡበትን ትችት ዝም ለማሰኘት በጀመረው ዘመቻም ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና ተማሪዎችን ለእስር ዳርጓል።
በሰቲት ጋዜጣ ላይ ካቀረባቸው ጽሑፎች መካከል የኤርትራን መንግሥት የሚተቹ እና ዴሞክራሲያዊ ለውጥ እንዲመጣ እንዲሁም የንግግር ነጻነት እንዲከበር የሚጠይቁ ይገኙበታል።
ጋዜጠኛ ዳዊት የፖለቲካ ተሃድሶን ከሚሹ ፖለቲከኞች የተላከ ግልፅ ደብዳቤ ካሳተመ በኋላም ነው ለእስር የተዳረገው።
ዳዊትን ጨምሮ በርካታ የግል ጋዜጣ አዘጋጆችም በጎሮጎሳውያኑ 2001 ለእስር ተዳረጉ።
ባለፈው ዓመት ጋዜጠኛ ዳዊት ፍርድ ቤት ለንግግር ነጻነት ባደረገው ትግል በስዊድን ተሸላሚ ሆኗል።
ኤርትራዊ እና ስዊድናዊው ጋዜጠኛ ዳዊት፣ 'ኤድልስታም' የተባለ ሽልማት የተበረከተለት "ልዩ ለሆነ ጀግንነቱ" እንደሆነ ተቋሙ በወቅቱ አስታውቆ ነበር።
ባለፈው ሳምንት የኤርትራ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ዕውቅና ከተሰጣቸው የክርስትና እምነት አብያተ ክርስቲያናት ውጪ አባል በመሆናቸው ለዓመታት ታስረው የቆዩ ወደ 98 የሚጠጉ ሰዎችን መልቀቁ ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪም ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጪ ከ18 ዓመታት በላይ ታስረው የነበሩ13 ሰዎች ከሦስት ሳምንት በፊት ተፈትተዋል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች አሥመራ አሁንም "ከ10,000 በላይ የሕሊና እስረኞችን" እንደያዘች ይገልጻሉ።















