በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው በአንድ ጀንበር 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ዘመቻ

የኢትዮጵያ መንግሥት በየዓመቱ የሚያካሂደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አንድ አካል የሆነው የችግኝ ተከላ ሂደት በአንድ ቀን 600 ሚሊዮን ችግኞችን የመትከል ዘመቻ በመላው አገሪቱ እየተካሄደ ነው።

ዛሬ አርብ ነሐሴ 17/2016 ዓ.ም. እየተካሄደ ባለው የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በምዕራባዊው የአገሪቱ ክፍል ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል አሶሳ ከተማ ተገኝተው ችግኞችን መትከላቸውን አሳውቀዋል።

በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ከፌደራል እና ከክልል ባለሥልጣናት ጀምሮ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በየአካባቢያቸው ችግኞችን እየተከሉ መሆናቸውን የመገናኛ ብዙኃን እየዘገቡ ነው።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት እንዳስታወቀው በዛሬው ዕለት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አማካይነት የሚተከሉት 600 ሚሊዮን ችግኞች ባለፉት አምስት ዓመታት በአገሪቱ የተተከሉትን ችግኞች ቁጥር ወደ 40 ቢሊየን ያደርሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመረሃ ግብሩ አማካከይነት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ችግኞችን መትከላቸውን ተከትሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት፣ በተመሳሳይ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ባለፈው ዓመት ከተተከሉት ችግኞች “50 ከመቶው በምግብ ዋስትና፣ አፈር ጥበቃ እና የመሬት መራቆት ላይ አስተዋፅዖ እንዲያደርጉ የተተከሉ” መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለዚህ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሚገኝበት የቤኒሻንጉል ክልል የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም እንደ አባይ ተፋሰስ ባሉ አካባቢዎች ችግኞችን በመትከል የውሃ ጥበቃ ሥራን ማጠናከር አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።