አሜሪካ ዘመናዊዎቹን ኤፍ-16 የጦር ጄቶች ለዩክሬን ለማስታጠቅ ፈቀደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ምዕራባውያን አጋሮቿ የእራሷ ስሪት የሆነውን ኤፍ-16 ተዋጊ ጄትን ጨምሮ እጅግ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖችን ለዩክሬን እንዲያስታጥቁ ልትፈቅድ መሆኑን ገለጸች።
የአሜሪካ የብሔራዊ ፀጥታ አማካሪ የሆኑት ጃክ ሰሊቫን እንዳሉት፣ ፕሬዝዳንት ባይደን ይህንን ውሳኔ ጃፓን ውስጥ እየተካሄደ ባለው የቡድን 7 ስብሰባ ላይ አርብ ዕለት “ለአቻዎቻቸው አሳውቀዋል።”
በተጨማሪም የአሜሪካ ወታደሮች የዩክሬን አቻዎቻቸው የጦር ጄቶቹን አጠቃቀም በተመለከተ ሥልጠና እንደሚሰጡ ሰሊቫን ገልጸዋል።
ከሩሲያ ጋር ጦርነቱ እየተባባሰ ከሄደበት ጊዜ አንስቶ ምዕራባውያን አጋሮቿ ዘመናዊ የጦር ጄቶችን እንዲያስታጥቋት ስትወተውት የቆየችው የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የአሜሪካን ውሳኔ “ታሪካዊ” ብለውታል።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም ለአጋሮቿ ያስታጠቀቻቸው ኤፍ-16 የተባሉትን ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖችን ለሌላ ወገን አሳልፈው መስጠት ከፈለጉ ፈቃዷን መጠየቅ እንዳለባቸው በሕግ ታስገድዳለች።
የአሁኑ የባይደን ውሳኔ ምዕራባውያን የጦር ጄቶቹን ለዩክሬን ለመስጠት በር የሚከፍትላቸው ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ለዩክሬን ሠራዊት ወሳኝ ጥንካሬን የሚሰጥ ነው።
ምዕራባውያን ባለፉት ወራት ከባድ መሳሪያዎች እና የአየር መከላከያ ሥርዓቶችን ለዩክሬን ለመስጠት የገቡትን ቃል መፈጸማቸውን ያስታወሱት ሰሊቫን፣ “አሁን ደግሞ ዩክሬን እራሷን እንድትከላከል ለማስቻል ባለን ዕቅድ መሠረት የአየር ኃይሏን ማሳሳል በምትችልበት ሁኔታ ላይ እየተወያየን ነው” ሲሉ ጃፐን ሄሮሺማ ውስጥ ተናግረዋል።
በቀጣይ ወራት ዘመናዊዎቹን የጦር ጄቶችን ለመጠቀም የሚያስችሉ ሥልጠናዎች እየተካሄዱ አውሮፕላኖቹን መቼ፣ ማን እና ምን ያህል ለዩክሬን እንደሚሰጡ ከውሳኔ ላይ እንደሚሰደረስ ገልጸዋል።
የምዕራባውያኑ ውሳኔ ዛሬ ቅዳሜ በይፋ የሚገልጽ ሲሆን፣ ወዳጆቿ የጦር አውሮፕላኖች እንዲያስታጥቋት ስትጠይቅ የቆየችው ዩክሬን ፕሬዝዳንት ውሳኔው “ሠራዊታችን በሰማይ ላይ ያለውን አቅም ያጠናክራል” በማለት ተግባራዊነቱ ላይ እንደሚወያዩ ተናግረዋል።
አሜሪካ ከጦር አውሮፕላኖች ውጪ ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን ስታስታጥቅ የቆየች ሲሆን፣ የጦር ጄቶችን እንደማትሰጥ ፕሬዝዳንት ባይደን ባለፈው የካቲት ገልጸው ነበር።
አሁን ግን ጦር ግንባር ዩክሬን የሚያስፈልጓት ነገሮች እየታዩ በአሜሪካ በኩል እንደሚሰጣት ጃክ ሰሊቫን ገልጸዋል። አሜሪካ ዩክሬን ዘመናዊ የጦር ጄቶች እንድትታጠቅ መፍቀዷ ጦርነቱ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየገባ መሆኑን ያሳያል እየተባለ ነው።
አሜሪካ ዩክሬን ዘመናዊ ጄቶቿን እንድትታጠቅ ብትፈቅድም፣ የኤፍ-16 ተዋጊ ጄቶችን የሚያበሩ ፓይለቶችን ማሰልጠን አስከ አራት ወራት የሚጠይቅ በመሆኑ አውሮፕላኖቹ በፍጥነት ወደ ጦርነቱ ላይገቡ ይችላሉ።
ኤፍ-16 የተባሉትን አሜሪካ ስሪት ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖችን በርካታ የአውሮፓ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የታጠቋቸው ሲሆን፣ የትኞቹ አገራት ጄቶቹን ለዩክሬን ለመስጠት ፈቃደኛ ይሆናሉ የሚለው ቀጣይ ጥያቄ ነው።
ኤፍ-16 የጦር ጄቶች የሌሏት ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ ኔዘርላንድስ እና ዴንማርክ የአሜሪካንን ውሳኔ ደግፈውታል።
አውሮፕላኖቹ ያላቸው ምዕራባውያን አገራት በቀዳሚነት አብራሪዎችን ለማሰልጠን ፈቃደኛ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ አስካሁን አውሮፕላኖቹን ለዩክሬን ለማስታጠቅ በይፋ ቃል የገባ አገር የለም።
እነዚህ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖች ለዩክሬን መሰጠት ጦርነቱን የበለጠ የሚያባብስ እና በቀጥታ ከሩሲያ ጋር ፍጥጫን የሚያስከትል ይሆናል በሚል ተቃውሞ እየገጠመው ነው።
የሩሲያ ወረራ በተጀመረበት ጊዜ አብዛኞቹ ሶቪየት ሰራሽ የሆኑ 120 ሚግ-29 እና ሱ27 የጦር አውሮፕላኖች የነበሯት ሲሆን፣ አምስት ወይም ስድስት እጥፍ የሚበልጡ የጦር አውሮፕላኖች ካሏት ሩሲያ ጋር ለመቀራረብ ዩክሬን አስከ 200 የሚደርሱ የጦር ጄቶች ያስፈልጓታል።
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ምዕራባውያን ወዳጆቻቸው ከድምጽ በሁለት እጥፍ ይፈጥናሉ የሚባሉትን እና በምድር እና በአየር ላይ ያሉ ኢላማዎችን መምታት የሚችሉትን በ1970ዎቹ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቁትን ኤፍ-16 አውሮፕላኖች እንዲያስታጥቋቸው ሲጠይቁ ቆይተዋል።
የጦር ባለሙያዎች እንደሚሉት እነዚህ ዘመናዊ የጦር አውሮፕላኖች ዩክሬን ከጦር ግንባሮች በስተ ጀርባ ያሉ የሩሲያ ኢላማዎችን ለመምታት ያስችሏታል።












