ዩናይትድ ኪንግደም ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ለዩክሬን ማስታጠቋን አረጋገጠች

‘ዘ ስቶርም ሻዶ’ የተባለውን የረጅም ርቀት ሚሳኤልን የታጠቀ የዩኬ ቶርኔዶ የጦር አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, CROWN COPYRIGHT

የምስሉ መግለጫ, ‘ዘ ስቶርም ሻዶ’ የተባለውን የረጅም ርቀት ሚሳኤልን የታጠቀ የዩኬ ቶርኔዶ የጦር አውሮፕላን

ዩናይትድ ኪንግደም ከጦር አውሮፕላኖች ላይ የሚወነጨፉ የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ላለችው ዩክሬን መስጠቷን አረጋገጠች።

አምራቹ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ተቋም እንደሚለው ይህ ‘ዘ ስቶርም ሻዶ’ በመባል የሚታወቀው የረጅም ርቀት ሚሳኤል 250 ኪሎ ሜትር የመጓዝ አቅም አለው።

ይህ ዩክሬን ዩናይትድ ኪንግደም እንድታስታጥቃት ስትጠይቅ የነበረው ሚሳኤል፣ አሜሪካ ከሰጠቻት ሂማርስ ሚሳኤል ጋር ሲነጻጸር ከሁለት እጥፍ በላይ ርቀት በመጓዝ ማጥቃት ይችላል።

ይህ የዩኬ የረጅም ርቀት ሚሳኤል የሩሲያን ወረራ ለመቀልበስ ሌላ ዙር መልሶ ማጥቃት ለማድረግ በዝግጅት ላይ ላለችው ዩክሬን አዲስ አቅምን የሚፈጥር ነው ተብሏል።

የረጅም ርቀት ሚሳኤሎቹ ከጦር አውሮፕላኖች ላይ የሚተኮሱ በመሆናቸው የዩክሬን አብራሪዎች ከጦርነት ግንባሮች በመራቅ ጥቃት መፈጸም ይችላሉ።

ሚሳኤሉ ከተተኮሰ በኋላ ከራዳር ዕይታ ውጪ ለመሆን ወደ ዝቅተኛ ከፍታ በመውረድ በጨረሮች እየተመራ ኢላማውን ለመምታት የሚያስችል አቅም አለው።

ዩኬ ሚሳኤሉን ለዩክሬን እየሰጠች መሆኑ ይፋ የተደረገው የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋላስ ምክር ቤት ቀርበው በተናገሩበት ወቅት ነው።

እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው ዩክሬን ምዕራባውያን አገራት ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች እንዲሰጧት በተደጋጋሚ ያቀረበችውን ጥያቄን ተከትሎ ነው።

ከጥቂት ወራት በፊት የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትር ኦሌክሲ ሬዝኒኮ በአውሮፓ ኅብረት ስብሰባ ላይ፣ አገራቸው የረጅም ርቀት ሚሳኤል የምታገኝ ከሆነ ሩሲያ ውስጥ ያሉ ኢላማዎችን ለመምታት አትጠቀምባቸውም ብለው ቃል ገብተዋል።

ባለፈው የካቲት ወር የዩኬው ጠቅላይ ሚኒስትር ሪሺ ሱናክ ለዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን ሊያስታጥቁ እየተዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረው ነበር።

“የዩክሬን ከተሞች በሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች እና በኢራን ድሮኖች ከሚፈጸሙባቸው ጥቃቶች በጋራ ልንከላከላቸው ይገባል” ሲሉ የተናገሩት ሱናክ፣ “ለዚህም ዩናይትድ ኪንግደም የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን በመስጠት የመጀመሪያዋ አገር ትሆናለች” በማለት ተናግረው ነበር።

ዩኬ ለዩክሬን የረጅም ርቀት ሚሳኤሎችን እያስታጠቀች መሆኑ ከተገለጸ በኋላ፣ የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ በሰጡት ምላሽ አገራቸው ዩክሬን ለምትጠቀማቸው ለእነዚህ ሚሳኤሎች “ተገቢውን” ወታደራዊ ምላሽ ትሰጣለች ብለዋል።

ለዩክሬን ተሰጠ የተባለው ‘ዘ ስቶርም ሻዶ’ የረጅም ርቀት ሚሳኤል ከዚህ በፊት የዩናይትድ ኪንግደም እና የፈረንሳይ አየር ኃይሎች በባሕረ ሰላጤው አካባቢ በኢራቅ እና በሊቢያ ውስጥ ጥቅም ላይ አውለውታል።

ዩኬ የምታመርተው ሚሳኤል ከአውሮፕላን ላይ ብቻ የሚወነጨፍ ሲሆን፣ ተመሳሳዩ የፈረንሳ ሚሳኤል ግን ከጦር መርከቦች እና ከሰርጓጅ መርከቦች ሊተኮስ ይችላል።