ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሲም ካርድ የማያስፈልገው አዲሱ አይፎን
አፕል በስማርት ስልኮች ምርት ገበያውን ሲመራ ሌሎች ደግሞ ይከተላሉ።
በዚህ ሳምንትም ይፋ ያደረገው አዲስ ምርቱ ከተለመደው ሲም ካርድ ውጭ የሚሰራ ሲሆን ወደፊት በሚኖሩ የስልክ ቴክኖሎጂዎች ላይ ሲም ካርድ ቦታዋ ምን ይሆናል የሚል ጥያቄን አስነስቷል።
ሁሉም የስልክ ተጠቃሚዎች ስልኮቻቸው እንዲሰሩ ትንሽየዋ ከፕላስቲክ የተሰራችውን ካርድ በስልኮቻቸው ውስጥ ማስገባት ይጠበቅባቸዋል።
ነገር ግን ለአይፎን ኤር ተጠቃሚዎች ይህ ያለፈ ታሪክ ይሆናል።
ስልኩ በኢሲም ብቻ የሚሠራ ሲሆን ይህም ተጠቃሚዎች ከአንዱ ኔትወርክ ወደ ሌላኛው ያለ ችግር እንዲደዋወሉ ወይም ሲምካርድ ለመቀየር መታገል ሳያስፈልጋቸው ከአንዱ የአገልግሎት አቅራቢ ወደ ሌላኛው በቀላሉ መቀየር ያስችላቸዋል።
ሲሲኤስ በተባለው ኩባንያ ውስጥ የሚሰራው ኬስተር ማን የተባለ የቴክኖሎጂ ባለሙያ አፕል ያስተዋወቀውን አዲሱን ምርቱን ተከትሎ "የሲም ካርድ የመጨረሻው መጀመርያ ነው" ሲል ተናግሯል።
ሁላችንም ያቺን ትንሽዬ ቺፕ አሽቀንጥረን ለመጣል ምን ያህል ዓመታት ይወስድብናል የሚለው ግን ገና ግልጽ አይደለም።
ሌላው አብሮ የተነሳው ጥያቄ ደግሞ ስልኮቻችንን የምንጠቀምበት መንገድ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል የሚለው ነው።
የእንግሊዘኛው ሲም (SIM) ተጠቃሚን ለመለየት የሚያገለግል ሞጁል ማለት ነው። ይህ በስልካችን ውስጥ የምናስገባው ካርድ ከኔትወርክ አቅራቢያችን ጋር የምንገናኝበት ዋነኛ ክፍል ነው።
በዚህም የተነሳ ጥሪ ማድረግ፣ የጽሑፍ መልዕክት መለዋወጥ እንዲሁም ዳታዎቻችንን መጠቀም እንችላለን።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢሲም (eSIM) አማራጭ ሆኖ የመጣ ሲሆን አዳዲስ ስልኮች የተለመደውን ሲም ካርድ ወይንም ኢሲም የመጠቀም ዕድል ነበራቸው።
ማክሰኞ ዕለት አይፎን ኤርን ያስተዋወቀው አፕል ስልኩ ኢሲምን ብቻ እንደሚጠቀም ይፋ አድርጓል።
ይህ ቀጭን እና አዲስ የአፕል ቤተሰብ የሆነው ስልክ በመላው ዓለም የኢሲምን ብቻ የሚጠቀም አይፎን ሆኖ በገበያ ላይ ይውላል።
በአሜሪካ የሚገኙ ተጠቃሚዎች እአአ ከ2022 ጀምሮ ኢሲም ብቻ የሚጠቀሙ ስልኮች ተገልጋይ ናቸው።
ይሁን እንጂ አይፎን ራሱ ሲምካርድን ላለመጠቀም አልወሰነም ነበር።
አይፎን 17፣ 17 ፕሮ፣ 17 ፕሮማክስ የተሰኙት የአይፎን አዳዲስ ምርቶች በሙሉ ኢሲም ብቻ የሚጠቀሙ ይሆናሉ ተብሏል።
ነገር ግን በሌሎች አገራት ሲምካርድ መቀበል እንዲችል አድርጎ ለገበያ እንደሚያቀርብ ተናግሯል።
ባለሙያዎች የስማርት ስልኮች ወደ አዲስ አቅጣጫ እየሄዱ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል።
ሲሲኤስ ኢንሳይት ይፋ ባደረገው ትንበያ መሰረት እአአ በ2024 ብቻ 1.3 ቢሊየን ኢሲም ያላቸው ስማርት ስልኮች ጥቅም ላይ ውለዋል።
ይህ ቁጥር በአውሮፓውያኑ 2030፣ 3.1 ቢሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል።
የ ፒፒ ፎርሳይት ቴክኖሎጂ ተንታኙ ፓውሎ ፔስካቶር "በጊዜ ሂደት ሲም መቀበያው ሙሉ በሙሉ እንደሚቀር ጠብቁ" ብለዋል።
የኢ-ሲም ጥቅም ምንድን ነው?
ፔስካቶር ወደ ኢሲም መሸጋገር "በርካታ ጥቅሞች" አለው ይላሉ። በግልፅ የሚታየው በስልክ ቀፎ ውስጥ ቦታ እንዲተርፍ ማድረጉ ባትሪን ትልቅ ለማድረግ ይረዳል።
ከዚህም ባሻገር የፕላስቲክ ሲም ካርዶችን አለመጠቀም ለአካባቢ ጥቅም አለው ያሉ ሲሆን፣ ሰዎች ወደ ውጭ አገራት ሲዘዋወሩ በርካታ አገልግሎት አቅራቢዎችን የማግኘት አማራጭን በመክፈት ከከፍተኛ ወጪ ይታደጋቸዋል።
ከስተር ማን በበኩላቸው አዲስ የአገልግሎት አቅራቢ እና ደንበኛ ግንኙነትን እንደሚፈጥር እምነት አላቸው።
ለምሳሌ ያህል ሰዎች ሲም ካርዳቸው መረጃ ለማግኘት ረጅም ርቀት ተጉዘው አገልግሎት አቅራቢያዎቻቸው ጋር በአካል አይገኙም ማለት ነው።
ለተጠቃሚዎች ጊዜ እና ገንዘብ የሚቆጥብ በመሆኑ ትልቅ ጥቅም ሊሆን ይችላል።
ይሁን እንጅ እንደ የትኛውም ለውጥ በሁሉም ሰው ቅቡልነት ላይኖረው ይችላል ይላሉ።
"ለውጡ በተለይም እድሜያቸው ለገፋ እና ቴክኖሎጂን ለመጠቀም እምብዛም በማይፈልጉ ሰዎች ተጨባጭ ጠቀሜታ አለው። ኢንዱስትሪው [ግን] ኢሲም እንዴት እንደሚሰራ በደንብ ማስረዳት ይኖርበታል" ብለዋል።