ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፌስቡክ እና ቲክቶክ ላይ የምናጠፋውን ጊዜ ለመቀነስ አማራጭ እየሆኑ ያሉት ‘የድሮ ስልኮች’
እንዲያው ሳይፈልጉት፤ ሳያስቡት ወይም ደግሞ ወደው እና ፈቅደው በዘመናዊ ስልክዎ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ . . ሌላም ሌላም የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ ሰፊ ጊዜዬን እያጠፋሁ ነው ብለው ያስባሉ?
ወይስ ማኅበራዊ ሚዲያ በመመልከት ጊዜዬን የማባክን ሰው አይደለሁም ብለው ያስባሉ?
ለዚህ ጥያቄ መልስ ከመስጠትዎ በፊት ወደ ሞባይል ስልክዎ ‘ሴቲንግ’ አምርተው ‘ስክሪን ታይም’ን ይመልከቱ።
ምናልባት በቀን ስልክዎን በመመልከት/በመነካካት የሚያሳልፉት ሰዓት ያልጠበቁት ሊሆን ይችላል።
ጠቃሚ የቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑት ዘመናዊ የእጅ ስልኮች ከዕለት ተዕለት ሕይወታችን ጋር ተያይዘው ልንላቀቃቸው የማንችላቸው ሱስ እየሆኑብን ነው።
የ16 ዓመቱ ካናዳዊ ሉክ ማርቲን፤ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ሳልጎበኝ ከቀረየሁ የሆነ ነገር ያመለጠኝ ይመስለኛል ይላል። “ሶሻል ሚዲያ አልመለከትም ብል እንኳ አይቻለኝም” ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
አንዳንዶች ከስልክ ጋር ያላቸውን ቁርኝነት ለመቀነስ ዘመናዊ ‘ስማርት ስልኮች’ ትተው ወደቀሙት ለመደወል እና ለጽሁፍ መልዕክት ለመላክ ብቻ ወሚውሉ ስልኮች ፊታቸውን እያዞሩ ነው።
በዩናትድ ኪንግደም የተሠራ አንድ ጥናት በአገሪቱ ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 7 ከሆናቸው ልጆች መካከል አንድ አራተኛው የራሳቸው የሆነ ስማርት ስልክ አላቸው።
በአንዳንድ ጥናቶች ደግሞ ማኅበራዊ ሚዲያን አብዝቶ መጠቀም በተላይ ደግሞ በልጆች የአእምሮ ጤና ላይ አሉታዊ ጉዳት ሊያመጣ እንደሚችል ተገልጿል።
አንዳንድ አክቲቪስቶች የስማርት ስልክ ተጠቃሚዎች ላይ የዕድሜ ገደብ ሊጣል ይገባል በማለት ልጆችን ከስማርት ስልክ ለማራቅ ይከራከራሉ።
እንደ ሉክ ያሉ ታዳጊዎች ግን በራሳቸው ፍቃድ ስማርት ስልካቸውን ዘመናዊ ባልሆኑት በቀደሙት ስልኮች እየቀየሩ ነው።
የሉክ አዲሱ ስልክ መደወል፣ የጽሑፍ መልዕክት መቀበል፣ ሂሳብ ማስላት እና የመሳሰሉ መሠረታዊ ግልጋሎቶችን ብቻ የሚሰጥ ነው።
“ጓደኞቼ አሁን ላይ በቀን ከ4 እስከ 5 ሰዓት ስልካቸው ላይ ናቸው። እኔም እንደዚያው ነበርኩ። አሁን ላይ ግን በቀን 20 ደቂቃ ብቻ ነው የምጠቀም።”
አዋቂዎችም ለራሳቸው፣ ለቤተሰባቸው እና ለሥራቸው ጊዜ ለመስጠት ሲሉ ስማርት ስልኮችን በቀደምት ስልኮች እየቀየሩ ነው።
የአምስት ዓመት ልጅ እናት የሆነችው ሊዚ ብራውተን በቅርቡ የድሮ ዓይነት ‘ተከፋች’ ኖኪያ ስልክ ገዝታ መጠቀም ጀምራለች።
“ከዚህ ቀደም የነበረኝን ማንነት ነው መልሼ ያገኘሁት። አሁን ከልጄ ጋር ጥሩ ጊዜን ማሳለፍ ችያለሁ” በማለት ታስረዳለች።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰሜን አሜሪካ ዘመናዊ ያልሆኑ ስልኮች ሽያጭ በከፍተኛ መጠን ጨምሯል። ሎስ አንጀለስ ከተማ በሚገኘው የሞባይል ስልክ መሸጫ ሱቅ ባለቤት የሆኑት ዴይዚ እና ዊል ደንበኞች ያሏቸውን አማራጮች እያስረዱ ነው።
“በጣም ብዙ ወላጆች ለልጆቻቸው በሚገዙላቸው የመጀመሪያ ስልክ ልጆች ያለ ገደብ ኢንተርኔትን እንዲያስሱ አይፈልጉም” ይላል ዊል።
የወላጆች ፍላጎት ይህ ቢሆንም አንዳንድ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሂደቱ አጋዥ የሆኑ መተገበሪያዎችን እንደ ግዴታ በማቅረባቸው ልጆችን ከስማርት ስልክ አርቆ ማቆየትን አስቸጋሪ እንዳደረጉት የአምስት ዓመት ልጅ ያላት ሊዝ ትናገራለች።
የሞባይል መሸጫ ሱቅ ባለቤቱ ዊል ለእንደነዚህ ዓይነቱ ችግር መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮች አሉ ይላል።
ዊል ልጆች ስማርት ስልኮችን ሲጠቀሙ አጠቃቀማቸውን መከታተል እና አንዳንድ መተግበሪያዎችን መገደብ የሚያስችሉ መተግበሪያዎች መኖራቸው ይገልጻል።
ከእነዚህ መካከል ደግሞ አንዱ ‘አንፕለክ ታግ’ (unpluq Tag) የተሰኘውን መተግበሪያ ይጠቅሳል። መተግበሪያው እንደ ማኅበራዊ ሚዲያ ያሉ መተግበሪያዎችን እንዲገድብ ካዘዝነው መተግበሪያዎቹን መከፍት የሚቻለው በገደብ ይሆናል ይላል።
በሰሜን አሜሪካ እና አውሮፓ ሰዎች ከስማርት ስልኮች እራሳቸውን እያራቁ መምጣቸውን ተከትሎ የስልክ አምራቾች በስማርት ስልክ እና ስማርት ባልሆኑ ስልኮች መካከል ያለ ሊባል የሚችል ስልክ አምርተው ለገበያ እያቀረቡ ነው።
ክሪስ ካስፓር ያቋቋመው ቴክለስ የተባለ ኩባንያ “ሆነ ብሎ ቀልብ የማይገዛ/አሰልቺ” የሆነ ስልክ ያመርታል። ይህ “ዋይዝፎን II” የሚባለው ስልክ ሲታይ አይፎን ይመስላል። ተግባሩ ግን ከአይፎን እጅጉን የራቃ ነው።
“በቀለማት የደመቁ መተግበሪያዎች የሉትም፣ መልክቶች ብቻ። ባለ ቀለም ስልክ አይደለም። ባለ ነጭ እና ጥቁር ቀለም ነው። ያለው የፊደል አጣጣል (ፎንት) አማራጭ ሁለት ብቻ ነው” ይላል ክሪስ ኩባንያው ስላመረተው ስልክ ሲናገር።
“ዋይዝፎን II” በስማርት ስልኮች ቅርጽ እና መጠን ይሠራ እንጂ ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የግድ ሊያስፈልጓቸው የሚችሏቸውን አማራጮች ብቻ ነው የያዙት።
ስልክ መደወል፣ የጽሁፍ መልዕክት መላክ፣ ካርታ (አቅጣጫ ጠቋሚ)፣ ሂሳብ የሚያሰላ፣ ካሜራ፣ ማስታወሻ መጻፊያ . . . እና የመሳሰሉት አገልግሎቶች ብቻ ነው ያሉት።
ክሪስ ይህን ስልክ ዲዛይን ሳደርግ በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለችውን ሴት ልጄን ከግምት በማስገባት ነው ይላል።
ይህ ስልክ ልጆችን እና አዋቂዎችን በእኩል ደረጃ በማገናዘብ መሥራቱን የሚገልጸው ክሪስ፤ ሰዎች ስማርት ስልኮቻቸው ላይ ረዥም ሰዓታትን በማሳለፋቸው ብዙ እያተረፉ የሚገኙ ግዙፍ ማኅበራዊ ሚዲያዎች እና የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች በምርታችን ደስተኛ አይደሉም ይላል።