ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከበረራ ፈቃድ እና ከቪዛ መመሪያ ጋር በተያያዘ በሶማሊያ እና በሶማሊላንድ ውዝግብ ተፈጠረ
ሶማሊያ እና ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ ባወጡት ተጻራሪ የበረራ ፈቃድ እና የቪዛ መመሪያ ምክንያት በሶማሊያ የአየር ክልል ውጥረት ነገሰ።
ይህ ክስተት አየር መንገዶችን እና መንገደኞችን ግራ ያጋባ ሲሆን፣ በርካታ መንገደኞችን ከጉዟቸው አስተጓጉሏል።
የሶማሊያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አየር መንገዶች ከሞቃዲሾ የኤሌክትሮኒክ ቪዛ (ኢ-ቪዛ) ያልያዙ መንገደኞችን ወደ ሶማሊላንድ ማጓጓዝ እንደማይችሉ ገልጾ፤ይህንን ሕግ የተላለፈ የበረራ እገዳ ሊያጋጥመው እንደሚችል ማስጠንቀቁ ተዘግቧል።
ባለሥልጣኑ በማስጠንቀቂያው በተለይ ፍላይዱባይን በመጥቀስ የሚያስተዳድረው ኤምሬት አየር መንገድ የፌደራል የኤሌክትሮኒክ ቪዛ ደንቦችን ችላ ብሏል ሲልም ከስሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶማሊላንድ ሲቪል አቪዬሽን እና አየር ማረፊያዎች ሚኒስቴር ያለ ፈቃድ ወደ ግዛቲቱ የአየር ክልል የሚገባ ማንኛውም አውሮፕላን ሕጋዊ እርምጃ እንደሚጠብቀው የሚገልጽ ሌላ መመመሪያ አውጥቷል።
ሚኒስቴሩ ሁሉም የሰላማዊ መንገደኞች እና የንግድ በረራዎች ወደ ግዛቷ ከመግባታቸው ወይም በአየር ክልሉ ከማለፋቸው በፊት ፈቃድ ማግኘት አለባቸው ብሏል።
ፈቃድ ያላገኘ ማንኛውም በረራ የሶማሊላንድን ሉዓላዊነት እንደጣሰ የሚቆጠር መሆኑን እና ሕጋዊ እርምጃ እንደሚጠብቀውም ሚኒስቴሩ አስጠንቅቋል።
ይህ የበረራ መመሪያ ከሰባት ቀናት በኋላ ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን፣ መመሪያው ሶማሊላንድ ግዛቷን፣ የውሃ አካሏን እና የአየር ክልሏን እንድቆጣጠር ይፈቅድልኛል ያለችውን የቺካጎ ሲቪል አቪዬሽን ስምምነትን ያከበረ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በአቪዬሺኑ ዘርፍ የ10 ዓመታት ልምድ ያላቸው እና በሐርጌሳ እና በሞቃዲሾ አየር ማረፊያዎች ያገለገሉት አብዲፈታህ ኦስማን ኢብራሒም እንደሚሉት ግን ሶማሊላንድ ዓለም አቀፍ የአገርነት እውቅና ስሌላት አሁን ላይ አውሮፕላኖች መመሪያዎቿን አክብረው በአየር ክልሏ እንዲያልፉ የሚያስገድድ ምንም ዓይነት የሕግ ማዕቀፍ የለም።
"ሶማሊላንድ አሁን ላይ የምትቆጣጠረው በግዛቷ በሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎች የሚያርፉትን ብቻ ነው። ሆኖም ቴክኒካዊ በሆነ መንገድ በአየር ክልሏ የሚያልፉትን ሁሉንም አውሮፕላኖች መከታተል ትችላለች" ብለዋል አብዲፈታህ።
ሆኖም አየር መንገዶች መመሪያዎቿን እና ትዕዛዞቿን እንዲከተሉ የምትጠይቅበት ምንም ሕጋዊ ሥልጣን እንደሌላት አብዲፈታህ አስረድተዋል።
ጨምረውም ሶማሊላንድ ሙሉ የአየር ክልሏን መቆጣጠር እና አውሮፕላኖች ደንቦቿን እንዲያከብሩ ከፈለገች፣ የአየር ክልል አስተዳደር ሥልጣኗን እንዲሁም የግዛቷን ሕግ ያላከበረ ማንኛውም አካል ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችላት ሕግ የማስፈፀም አቅም ሊኖራት ይገባል ብለዋል።
አሁን ላይ ሁለቱ ወገኖች ያወጡት የተለያየ መመሪያ ሶማሊያ ደርሰው ወደ ሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ እንዲሁም ወደ ሌሎች ክልሎች የሚጓዙ ዓለም አቀፍ መንገደኞች እና የውጭ ዜግነት ያላቸው መንገደኞችን ግራ አጋብቷል።
በመመሪያው መሠረት ለኦንላይን ቪዛ ከፍሎ ሶማሊያ የገባ መንገደኛ ፑንትላንድ፣ ቦሳሶ ለመጓዝ ተጨማሪ የቪዛ ክፍያ መፈጸም ይጠበቅበታል።
ሶማሊያ እና ሶማሊላንድ ለአየር መንገዶች መመሪያ ያወጡት በመካከላቸው ያለው ውጥረት ባየለበት ወቅት ነው።
ከአቪዬሽን ጋር በተያያዘ ከሚያጋጥሙ ክስተቶች ጋር በተያያዘ እርስ በእርሳቸው ሲካሰሱ መስማት አዲስ አይደለም።
ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ የሶማሊላንድ አቪዬሽን በሶማሊያ የአየር ክልል ውስጥ ሲበር የነበረ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ከሌላ አቅጣጫ ሲመጣ ከነበረ የኳታር አውሮፕላን ጋር ለተፈጠረው "ለግጭት ሊዳርግ የሚችል" ሁኔታ የሶማሊያን የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎችን ከስሶ ነበር።
"አውሮፕላኖቹ በተመሳሳይ ከፍታ ላይ እየበረሩ የነበሩት በሞቃዲሾ የሚገኙ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች በሰጡት የተሳሳተ መረጃ ነው" ነበር ያለው።
የሶማሊያ አቪዬሽን ባለሥልጣን በበኩሉ "በሁለቱ አውሮፕላኖች መካከል የነበረው ርቀት ስጋት ላይ የሚጥል አይደለም" ሲል አስተባብሏል።
ሁለቱ ወገኖች ከአየር ክልል ጋር በተያያዘ ለወራት ሲወዛገቡ የቆዩ ሲሆን፣ አሁን ላይ ያወጡት ተጻራሪ የበረራ እና የቪዛ መመሪያ በመንገደኞች እና በአየር መንገዶች ላይ ግራ መጋባትን እና መስተጓጎልን ፈጥሯል።
ሶማሊላንድ ባለቤትነቱ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መንግሥት የሆነው ፍላይዱባይ ሕጓን የማያከብር ከሆነ ወደ ግዛቷ እንዳይገባ ልትከለክል እንደምትችል በማስጠንቀቅ ወደ ግዛቷ ለሚያደርጋቸው በረራዎች የኤሌክትሮኒክ ቪዛ መጠየቁን እንዲያቆም የ15 ቀናት ቀነ ገደብ መስጠቷን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ግዛቷ ይህን የጊዜ ገደብ ያስቀመጠችው ሶማሊያ መስከረም ወር ላይ የጉዞ ሥርዓትን ለማሳለጥ፣ ፀጥታን ለማጠናከር እና የኢሚግሬሽን አገልግሎትን ለማዘመን በሚል ያወጣችውን አዲስ የኤሌክትሮኒክ ቪዛ ሥርዓት ውድቅ ማድረጓን ተከትሎ ነው።
ወደ አካባቢው ከሚበሩ አየር መንገዶች መካከል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይገኝበታል።
በግል የሚተዳደረው ካብ ቴሌቪዥን እንደዘገበው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ሐርጌሳ የሚጓዙ መንገደኞች የኤሌክትሮኒክ ቪዛ ማቅረብ ያለባቸውን መስፈረት በመተው በሶማሊላንድ ባለሥልጣናት የተቀመጡትን መመሪያዎች አክብሯል።
የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ግን ሶማሊላንድን ጨምሮ ወደ የትኛውም የአገሪቷ ክፍል የሚጓዙ መንገደኞች በኦንላይን ቪዛ ማመልከት እንዳለባቸው አፅንኦት ሰጥቷል።
ሶማሊላንድ እንደ አውሮፓውያኑ ከ1991 አንስቶ ነጻነቷን ብታውጅም ሶማሊያ የምትቆጥራት የራሷ ግዛት አካል አድርጋ ነው።
በዚህም ምክንያት የበረራ የአየር ክልልን እና ወደብን ጨምሮ በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለው ውዝግብ ለአስረተ ዓመታት ዘልቋል።
ጥቅምት ወር ላይ የሶማሊላንድ ፕሬዚዳንት አብዲራህማን ኢሮ አስተዳደራቸው ከሶማሊያ ጋር "ጦርነት ውስጥ እንዳልገቡ" የገለጹ ሲሆን፣ ነገር ግን ሁለቱ ወገኖች ፓስፖርት፣ የአቪዬሽን መብቶችን እና ዓለም አቀፍ አገራዊ መለያ ቁጥር (ኮድ)ን ጨምሮ እንደሚጋሩ ገልጸዋል።