የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ወደ ሞስኮ አቅንተው ከቱፒን ጋር ሊወያዩ ነው

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ በቀጣይ ሳምንት ወደ ሞስኮ አቅንተው ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር እንደሚገናኙ ይፋ ተደረገ።

የሩሲያ መንግሥት ፑቲን እና ዢ “በአጠቃላይ አጋርነት እና በስትራቴጂካዊ ትብብር ዙሪያ” ይነጋገራሉ ብሏል።

ጉብኝቱ የሚካሄደው የሩሲያ አጋር የሆነችው ቻይና የዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም ላቀረበችው ምክረ ሃሳብ ምዕራባውያን ጀርባቸውን ከሰጡ በኋላ ነው።

ምዕራባውያኑ ቤይጂንግ የጦር መሳሪያዎችን ለሞስኮ ከመስጠት እንድትቆጠብ ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ፕሬዝዳንት ዢ በፑቲን ግብዣ ከሰኞ የካቲት 11 እስከ 13/2015 ዓ.ም. ድረስ በሞስኮ ቆይታ እንደሚያደርጉ አስታውቋል።

“የወዳጅነት እና የሰላም” በተባለው ጉብኝት ሁለቱ መሪዎች ሲገናኙ በርካታ የሁለትዮሽ የትብብር ሰነዶች እንደሚፈረሙ ይጠበቃል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ ሁአ ቹኚንግ አገራቸው በዩክሬን ጦርነት ለየትኛውም ወገን ያላደላ አቋም እንዳላት ገልጸዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ ጦርነቱን ለማስቆም የቻይና ምክር ሃሳብ ላይ ከዢ ጋር ተገናኝተው መምክር እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር።

“ቻይና ለሩሲያ ጦር መሳሪያ አትሰጥም የሚል የጸና እምነት እንዲኖረኝ ፈልጋለሁ” ብለው ነበር ዜሌንስኪ።

ምንም እንኳ በቻይና ባለሥልጣናት ባይረጋገጥም ዢ የሩሲያ ጉብኝታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ከዜሌንስኪ ጋር በቴሌ ኮንፍረንስ ይገናኛሉ የሚሉ መረጃዎችን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን እያወጡ ነው።

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚይትሮ ኩሌባ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከዢ ጋር በስልክ ለመነጋገር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ሩሲያ በዩክሬን እያደረገች ያለችውን ጦርነት ለመደገፍ ቻይና ጦር መሳሪያ እና ተተኳሽ ለመስጠት እያጤነች ነው ብለው ነበር።

የቻይና ኩባንያዎች ወታደራዊ ያልሆኑ ድጋፎችን ቀድሞውኑ ለሩሲያ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው፤ አሁን ላይ አሜሪካ ያላት መረጃ ቤይጂንግ ወታደራዊ ድጋፍ ልታደርግ እንደምትችል ነው ብለዋል።

ቻይና ግን ይህን የአሜሪካን ክስ አጥብቃ ተቃውማለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት ሐሙስ መጋቢት 7/2015 ዓ.ም. ኪዬቭ እና ሞስኮ ግጭት ለማቆም ዳግም የሰላም ንግግር በአስቸኳይ መጀመር አለባቸው ብሏል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኪን ጋንግ ከዩክሬኑ አቻቸው ኩሌባ ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር ሁለቱም ወገኖች እራሳቸውን ከግጭት ቆጥበው በአፋጣኝ የሰላም ንግግር ማድረግ አለባቸው ተብሏል።

ኩሌባ ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር በግዛት አንድነት መርህ መከበር አስፈላጊነት ላይ መምክራቸውን ገልጸዋል።