ትራምፕ ኩባ ላይ የጣሏቸውን ማዕቀቦች ባይደን ሊያላሉ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኩባ ላይ የጣሏቸው ከባድ ማዕቀቦችን የማላላት ዕቅድ እንዳለ ተገለጸ።
ኩባውያን ሠራተኞች ወደ አገራቸው የሚልኩት ገንዘብ እና ወደ ኩባ የሚደረግ ጉዞ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች ሊላሉ እንደሚችሉ የጆ ባይደን አስተዳደር አስታውቋል።
አሜሪካ የኩባውያንን የቪዛ ጥያቄ የምትገመግምበት ፍጥነትም ይጨምራል ተብሏል።
የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባዩ ኔድ ፕራይስ እንዳሉት፣ ይህ ውሳኔ ኩባውያን "ከመንግሥት ጭቆና ነጻ የሆነ" ሕይወት እንዲመሩ ያስችላል።
ኩባውያን ሠራተኞች ከአሜሪካ ወደ ኩባ በየሦስት ወሩ ከ1000 ዶላር በላይ እንዲልኩ አይፈቀድም ነበር።
የአሜሪካ ባለሥልጣኖች እንዳሉት የገንዘብ ዝውውሩ ከዚህ በኋላ ቢፈቀድም "ሰብአዊ መብት የሚጥሱ እጅ እንዳይገባ መደረግ አለበት"።
ከሀቫናው የኮምኒስት መንግሥት ጋር ግንኙነት ያላቸውና አሜሪካ ጥቁር መዝገብ ውስጥ የከተተቻቸው ተቋሞች ከዚህ ቀደም ተጥሎባቸው የነበረው እገዳ አይነሳላቸውም።
ሆኖም ግን ወደ ሀቫና ተጨማሪ በረራዎች ይፈቀዳሉ። ቤተሰቦችም ዳግመኛ እንዲገናኙ ይደረጋል።
ባራክ ኦባማ በአሜሪካ እና በኩባ መካከል ያለውን ውጥረት ቢያረግቡም ዶናልድ ትራምፕ ከ2017 ወዲህ የተለያዩ ማዕቀቦች ጥለዋል።
ከእነዚህ መካከል የቪዛ ሂደት መጓተት፣ ሠራተኞች ወደ አገር ቤት ገንዘብ እንዳይልኩ ማድረግ እና አሜሪካውያን ከቤተሰብ ጥየቃ ውጭ ወደ ኩባ እንዳይሄዱ መከልከል ይጠቀሳሉ።
ትራምፕ ማዕቀብ የጣሉት የኩባን መንግሥት "ጨካኝ" ካሉ በኋላ ነው። ኦባማ ከኩባ ጋር ስምምነቶች መፈራረማቸውንም ተችተዋል።
የኩባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማዕቀቦች መላላታቸው "ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ የሚደረግ አንድ እርምጃ ነው" ብለዋል።
ሆኖም ግን በ1962 የተጣለውን እገዳ እንደማያሻሽል ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የባይደን ዴሞክራት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ቦብ መነንዴዝ ማዕቀቦቹ መላላታቸውን ተቃውመዋል።
"ጨካኙ የኩባ መንግሥት ዜጎቹን አንገላቷል። ማዕቀቦችን ማላላት የተሳሳተ መልዕክት ይልካል" ሲሉ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
ሴናተር ማርኮ ሩቢዮም "ይህ ውሳኔ ወደከሸፈው የኦባማ ዘመን ይመልሰናል" ብለዋል።
ማዕቀቦች በመላላታቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ኩባውያን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ዳግመኛ ይገናኛሉ።
ትራምፕ ከ2016 በኋላ በርካታ ምጣኔ ሀብታዊ ማዕቀብ ጥለዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና የምጣኔ ሀብት መሽመድመድ ኩባን እየፈተናት ይገኛል።












