ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሊቨርፑል እና የማን ዩናይትድ ደጋፊዎች ልጁን በሞት ላጣው ሮናልዶ ድጋፋቸውን ገለጹ
የማንቸስተር ዩናይትድ እና የሊቨርፑል ደጋፊዎች ህጻን ልጁን በሞት ላጣው ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና ለቤተሰቡ በአንፊልድ ለአንድ ደቂቃ ድጋፋቸውን ገልጸዋል።
ተጨዋቹ የሚታወቅበትን ሰባት ቁጥር ምክንያት በማድረግ የሊቨርፑል ደጋፊዎች የክለባቸውን መዝሙር 'You'll Never Walk Alone' ሰባተኛው ደቂቃ ላይ ዘምረዋል።
የሁለቱም ቡድን ደጋፊዎች ከመቀመጫቸው ተነስተው ለአንድ ደቂቃ ቆመው አጨብጭበዋል። የሮናልዶ ስም እና ቁጥር የያዘ የዩናይትድ ማሊያም ከፍ ተደርጎ ተይዟል።
ሮናልዶ እና አጋሩ ጆርጂና ሮድሪጌዝ የሕፃን ልጃቸውን ህይወት ማለፍ ይፋ ያደረጉት በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነበር ። ጥንዶቹ የልጃቸውን በሞት መነጠቅ "ማንም ወላጅ ሊሰማው የሚችለው ትልቁ ህመም" ሲሉ ገልጸውታል።
የ37 ዓመቱ ሮናልዶ እና የ28 አመቷ ሮድሪጌዝ መንታ ልጆችን እየጠበቁ ነበር።
ከመንትዮቹ መካከል ሴት ልጃቸው በሕይወት የተረፈች ሲሆን የእሷን መወለድም "ይህን ጊዜ በተወሰነ ተስፋ እና ደስታ ለመኖር የሚያስችል ጥንካሬ ይሰጠናል" ሲሉ ገልጸውታል።
ሮናልዶ እና ባለቤቱ "ልጃችን አንተ የእኛ መልአክ ነህ። ሁልጊዜም እንወድሃለን" ብለው ጽፈዋል።
የዩናይትድ እና የሊቨርፑል ተጫዋቾች ወደ ሜዳ የገቡት ለሮናልዶ እና ለቤተሰቡ ክብር ሲሉ ጥቁር ጨርቅ ክንዳቸው ላይ አስረው ነበ ።
ፖርቹጋላዊው ተጫዋች ትናንት ማክሰኞ ምሽት የተካሄደው የሁለቱ ተቀናቃኞች ጨዋታ አምልጦታል።
በትናንቱ ምሽት ኃያልነቱን የያዘው ባለ ሜዳው ሊቨርፑል፤ 4 ለ 0 በማሸነፍ የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መምራት ከቻለበት ጨዋታ በፊት የዩናይትዱ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ራልፍ ራይኒክ በሕይታችን ውስጥ ከእግር ኳስ የሚበልጡ ብዙ ነገሮች አሉ ሲሉ ተደምጠዋል።
"መላው ቡድን፣ መላው ክለብ ከእሱ [ሮናልዶ] ጋር ነው" ሲሉም ራንኒክ አክለዋል።
የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ በበኩላቸው የሮናልዶን ህፃን ልጅ ለማስታወስ የተደረገውን ጭብጨባ "የጨዋታው ዋና መልዕክት" ብለውታል።
"የክርስቲያኖ እና የቤተሰቡን ሃዘን እንጋራለን" ብለዋል ክሎፕ።
"ከተቀናቃኝነት በዘለለ እግር ኳስ እንደዚህ መሆን አለበት። ክብርን ማሳየት ብቸኛው አስፈላጊ ነገር ነው። ዜናውን ከሰማን በኋላ የሁላችንም ሃሳብ ከሮናልዶ እና ቤተሰቡ ጋር ነው" ብለዋል።
"እንዴት ሊሆን እንደሚችል መገመት እንኳን አልችልም። በእውነት እናዝናለን" ሲሉ ገልጸዋል።
በጨዋታው ዙሪያ በቀጥታ አስተያየት ሲሰጥ የነበረውና የቢቢሲ ሬድዮ 5 የእግር ኳስ ጋዜጠኛ ጆን መሪ የነበረውን ድባብ "አስደናቂ" ሲል ገልጾታል።
"በእውነቱ በጣም አስደናቂ ነበር። ከሰው ወደ ሰው የተደረገ ድንቅ ድጋፍ" ብሏል።
የቀድሞው የኤቨርተን እና የስኮትላንድ አጥቂ ጄምስ ማክፋደን ከሊቨርፑል ደጋፊዎች የተሰጠውን ድጋፍ 'የእውነተኛ ማንነት ማሳያ' ሲል ገልጿል።
አክሎም "በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ለክርስቲያኖ ሮናልዶ ያላቸውን ክብር እና ድጋፍ ማሳየታቸው ያላቸውን ምርጥ ማንነት ያሳያል" ብሏል።