ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በኢትዮጵያ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ ውሳኔ ተላለፈ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 25/2014 ዓ.ም ያጸደቀውና ለስድስት ወራት በመላው ኢትዮጵያ ተጥሎ የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ በዛሬው ዕለት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ውሳኔ አሳልፏል።
ምክር ቤቱ ዛሬ ጥር 18/2014 ዓ.ም ባካሄደው 2ኛው አስቸኳይ ስብሰባው ነው ለስድስት ወራት ተጥሎ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሦስት ወራት በማይሞላ ጊዜ እንዲነሳ ውሳኔ ላይ የደረሰው።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲያጥር ምክንያት የሆነውም ለአገሪቱ ስጋት የነበረው" የአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት አደጋ" መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ መድረሱ መሆኑም ተገልጿል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም ህወሓት እና አጋሮቹ የአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ላይ የደቀኑትን አደጋን ለመከላከል እንዲያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014ን ያወጀ ሲሆን፣ ይህ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በአዋጅ ቁጥር 1264/2014 መጽደቁ ተገልጾ ነበር።
አዋጁ በጸደቀበትም ወቅት በአገሪቱ የተደቀነውን የህልውናና እና የሉዓላዊነት አደጋ በመደበኛው የህሕ ማስከበር ሥራ መከላከል የማይቻል ሆኖ በመገኘቱም እንደነበር ተጠቅሷል።
በአሁኑ ወቅት ያለውን ስጋት በመደበኛው የሕግ ማስከበር ተግባር መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈፃሚነት ጊዜ ማሳጠር አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱም ተገልጿል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወራት የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ምክንያት የሆኑ ሁኔታዎች ከተቀየሩ እና በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳዮችን መቆጣጠር ይቻላል ብሎ ካመነ የስድስት ወር ጊዜው ሳይጠናቀቅ ጊዜውን የማሳጠር ሥልጣን እንደተሰጠውም ተጠቅሷል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የአዋጁን ተፈጻሚነት እንዲቀር የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤትተወያይቶ በማጽደቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል።
በወቅቱም በአስቸኳይ አዋጁ ጊዜ የሚወሰዱ እርምጃዎች ተብለው ከተጠቀሱትም መካከል በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል መከላከያ ኃይልን ወይም የትኛውንም ሌላ የፀጥታ አካል በማሰማራት ሰላምና ፀጥታ እንዲያስክብሩ ትዕዛዝ መስጠት፣ የሰዓት ዕላፊ ገደብ መወሰን፣ ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ሥር ለማድረግ፣ ይህ አዋጅ ተፈጻሚ ሆኖ ባለበት ጊዜ ድረስ ይዞ ለማቆየት ወይም በመደበኛ ሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል።
በተጨማሪም ከሽብር ቡድኖች ጋር ይተባበራል ብሎ ምክንያታዊ በሆነ መልኩ የተጠረጠረ ማንኛውንም ሰው ወይም ድርጅት ንብረት የሆነን ማንኛውንም ቤት፣ ህንጻ፣ ቦታ፣ መጓጓዣ ለመበርበርና እንዲሁም ማንኛውንም ሰው ለማስቆም፣ ማንነቱን ለመጠየቅ፣ ለመፈተሽ ይችላል፤ በብርበራ ወይም በፍተሻ የተያዙ የጦር መሳሪያዎችን መውረስ ይችላል የሚሉ ተካትተውበታል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመላው ኢትዮጵያ ተግባራዊ በሆነባቸው ባለፉት ወራት ጋዜጠኞችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውና ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ እየተፈቱ መሆናቸው ይታወቃል።