ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሲኒማቶግራፈሯን የገደለው ዝነኛው ተዋናይ ሽጉጡ ጉዳት እንደማያደርስ ተነግሮት ነበር
ዝነኛው ተዋናይ አሊክ ባልደዊን በቀረጻ ወቅት የተሰጠው ሽጉጥ ጉዳት እንደማያደርስ እንደተነገረው አንድ የፍርድ ቤት ሰነድ አመለከተ።
ተዋናዩ በፊልም ቀረጻ ወቅት የተሰጠውን ሽጉጥ ከተኮሰ በኋላ በሥራ ላይ የነበረችውን የሲኒማቶግራፈሯ ሀሊይና ሀቸንስ ህይወት አልፏል። ከጀርባዋ ቆሞ የነበረው የፊልሙ አዘጋጅ ጆኤል ሶውዛ ደግሞ ቆስሏል።
የፍርድ ቤት ሰነድ እንደሚያሳየው የፊልሙ ተባባሪ አዘጋጅ ነው ሽጉጡን ለአሊክ የሰጠው። ሲሰጠውም ሽጉጡ እውነተኛ ጥይት እንደሌለውና ጉዳት እንደማያደርስ ነግሮታል ተብሏል።
ሽጉጡ ውስጥ ጥይት ስለመኖሩ ተባባሪ አዘጋጁ እንዳላወቀም ተገልጿል።
አሊክ 'ረስት' በተባለው ፊምል በቀረጻ ወቅት ሽጉጡን ሲተኩስ ሀሊይናን ደረቷ ላይ መቷት ሕይወቷ አልፏል።
የኒው ሜክሲኮ፣ ሳንታ ፌይ ፖሊስ ደም የነካውን የአሊክ ልብስ እና ሽጉጡን ለምርመራ ወስዷል።
የ63 ዓመቱ ተዋናይ አሊክ በፖሊስ ምርመራ እየተደረገበት ቢሆንም እስካሁን ማንም ላይ ክስ አልተመሠረተም።
የፊልሙ መሪ ተዋናይ እና ፕሮዲውሰሩ አሊክ "በሀሊይና ሞት ልቤ ተሰብሯል። ለባለቤቷ፣ ለልጇ እና ለሚወዷት ሰዎች በአጠቃላይም አዝኛለሁ። በተፈጠረው አሳዛኝ አጋጣሚ ምን ያህል እንደደነገጥኩ እና እንዳዘንኩ የምገልጽበት ቃላት የለኝም" ሲል በትዊተር ገጹ ጽፏል።
ለፖሊስ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ እንደሆነም ተዋናዩ ተናግሯል።
የ42 ዓመቷ ሲኒማቶግራፈር የተወለደችው ዩክሬን ነው። ሎስ አንጀለስ ውስጥ ፊልም ያጠናች ሲሆን እአአ በ2019 በአሜሪካ ሲኒማቶግፈር መጽሔት "እያደገች ያለች ኮከብ" የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷት ነበር።
'ረስት' የተባለው ፊልም በሚቀረጽበት ቦታ ላይ የነበሩ ሠራተኞች የቀረጻ ሁኔታው ምቹ አይደለም ብለው ሥራ ባቋረጡ በሰዓታት ውስጥ ነበር ተኩሱ የተፈጸመው።
ቀረጻው በሚካሄድበት ወቅት የፊልሙ ሠሪዎች ሆቴል ውስጥ እንደሚያርፉ ቢነገራቸውም ይህ ባለመደረጉ በየቀኑ 80 ኪሎ ሜትር ለመንዳት መገደዳቸውን ገልጸው ሥራ ያቆሙት።
አሊክ ሽጉጡን በተኮሰበት ቀን የሽጉጦችን ደኅንነት የማጣራት ኃላፊነት የተሰጣት በ20ዎቹ ዕድሜ ያለች አዲስ ባለሙያ መሆኗን ቢቢሲ አረጋግጧል።
አሊክ ፊልሙ ላይ የልጅ ልጁ በድንገት ሰው ገድሎ ሞት የተፈረደበትን ሰው ወክሎ ይተውናል።
በይበልጥ የሚታወቀው '30 ሮክ' በተባለው አስቂኝ ተከታታይ ፊልም ሲሆን ሳተርደይ ናይት ላይቭ ላይ ዶናልድ ትራምፕን ሆኖ በመጫወትም ይታወቃል።