ዕጮኛውን አንቆ ሳይገድል አይቀርም ተብሎ የተጠረጠረው ወጣት አስክሬን ተገኘ

በተፈፀመባት ግድያ ምክንያት የብዙዎች መነጋገሪያ ሆና የቆየችው ጦማሪ ዕጮኛ ሬሳ ፍሎሪዳ ካለ አንድ መናፈሻ ውስጥ መገኘቱን ኤፍቢአይ አስታወቀ።

ከአንድ ወር በላይ የገባበት ጠፍቶ የቆየው ብራያን ሎንድሪ ሬሳ የተለየው በጥርሱ አማካኝነት ነው።

ብራያንና ዕጮኛው ጋቢ ፔቲቶ ባለፈው ወር ለሽርሽር ከወጡ በኋላ ብራያን ብቻውን ወደ ፍሎሪዳ መመለሱን ተከትሎ ግድያውን ፈፅሟል የሚል ጥርጣሬ ነበር።

የጦማሪዋ ጋቢ ሬሳ የተገኘው ለሽርሽር የሄዱበት ዋዮሚንግ ግዛት ውስጥ ነበር። በጋቢ ግድያ ተጠርጣሪ የነበረው ብራያን በፖሊስ ሲፈለግ ቆይቷል።

ኤፍቢአይ ሐሙስ ዕለት በለቀቀው መግለጫ የሟቹን ግለሰብ ጥርስ በመመርመር ግለሰቡ ብራያን ሎንድሪ መሆኑን አረጋግጠናል ብሏል።

የግለሰቡን ቤተሰቦች የሚወክል አንድ ጠበቃ በለቀቀው መግለጫ ደግሞ የብራያን እናትና አባት የልጃቸውን ሞት መረዳታቸውን አስታውቋል።

የፍሎሪዳ ባለሥልጣናት ረቡዕ ዕለት ነበር ከአንድ ፓርክ ውስጥ ሬሳ ማግኘታቸውን ይፋ ያደረጉት።

ብራያን ከተሰኘው ግለሰብ ሰውነት ጋር ንብረትነቱ የእርሱ መሆኑ የተረጋገጠ የጀርባ ቦርሳና ማስታወሻ ደብተር በፍለጋ ተገኝቷል።

ኤንቢሲ የተሰኘው የዜና ጣቢያ በፍለጋው ወቅት አጥንቶችና የራስ ቅል መገኘቱን ዘግቧል።

ብራያን ማነው?

የ22 ዓመቷ ጦማሪ ጋቢ ፔቲቶና የ23 ዓመቱ ጓደኛዋ ብራያን ጉዳይ አሜሪካን ሲያነጋግር ሰንብቷል።

ጥንዶቹ በብሔራዊ ፓርኮች እየተዘዋወሩ ያሳለፉትን ሽርሽር በማሕበራዊ ድረ-ገፆቻቸው ለወዳጆቻቸው ሲያጋሩ ነበር የከረሙት።

ነገር ግን የጋቢ ቤተሰቦች ልጃቸውን ከነሃሴ መጨረሻ ጀምሮ ሊያገኟት ባለመቻላቸው መስከረም 1 ቀን ጠፍታብናለች ሲሉ ለፖሊስ አመለከቱ።

ይሄኔ ነው ዕጮኛዋ ብራያን ጋቢን ትቶ ወደ ፍሎሪዳ መመለሱ የተደረሰበት። የጋቢ ቤተሰቦች ዕጮኛዋና ቤተሰቦቹ በልጃቸው ፍለጋ ጉዳይ ትብብር እንዲያደርጉ ቢጠይቁም ብራያንም ጠፋ።

የብራያን ቤተሰቦች ልጃቸውን ለመጨረሻ ጊዜ ያዩት መስከረም 3 ተራራ ለመውጣት ብቻውን ከቤት ሲወጣ እንደሆነ ለፖሊስ ተናገሩ።

ይኼኔ የጥንዶቹ ቤተሰቦች አንድ ላይ ሆነው የልጆቻቸውን ዱካ ለማግኘት ፍለጋ ወጡ።

የጋቢ ሬሳ መስከረም 8 ዋዮሚንግ ግዛት ውስጥ ተገኘ። የሬሳ ምርመራው እንደሚያሳየው ጋቢ ሕይወቷ ያለፈው አንገቷ ታንቆ ሲሆን አስከሬኗ ከመገኘቱ በፊት ለሳምንታት ጫካ ውስጥ ቆይቷል።

ምንም እንኳ ብራያን በዕጮኛው ግድያ በኤፍቢአይ ተጠርጥሮ ባይያዝም ከጋቢ ሞት በኋላ የባንክ ተንቀሳቃሽ ካርዷን በመጠቀም የእስር ትዕዛዝ ወጥቶበት ነበር።

የብራያን የጀርባ ቦርሳ ነው የተባለውን ንብረት ያገኙት ፍለጋውን የተቀላቀሉት አባቱ ነበሩ።

የብራያን ቤተሰቦች ጠበቃ የሆኑት ስቲቭ ቤርቶሊኖ የብራያን ቤተሰቦች ሬሳው ተገኘ የተባለበት ቦታ መረጃውን ቀብረው ነው እየተባለ የሚወራው ሃሰት ነው ሲሉ ለሲኤንኤን ተናግረዋል።