የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት የቀድሞውን የትራምፕ ረዳት በሕግ ለመጠየቅ ተስማሙ

ታኅሣሥ 28 የተፈጠረውን የካፒቶል አመጽ የሚመረምረው የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ኮሚቴ የዶናልድ ትራምፕን የቀድሞ ከፍተኛ ረዳት ኮንግረሱን በመናቅ እንዲጠየቅ በአንድ ድምፅ ድጋፍ ሰጥቷል።

ስቲቭ ባነን በኮሚቴው ፊት እንዲመሰክር ቢጠራም ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ ነበር።

ሙሉው ምክር ቤት ሐሙስ ዕለት በጉዳዩ ከተስማማ ክስ የመክፈት የመጨረሻ ውሳኔ ወደሚሰጠው የፍትሕ ቢሮ ይላካል።

ባነን ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የገንዘብ ቅጣት እና እስከ አንድ ዓመት እስራት ሊጠብቀው ይችላል።

የቀድሞው የትራምፕ ዋና ስትራቴጂስት በመሆን ያገለገለው ባነን በዘጠኝ የምክር ቤት አባላት ትናንት በተሰጠው ድምጽ ላይ በይፋ አስተያየት አልሰጠም።

የኮሚቴው አባልት የሆኑት ሁለት ሪፐብሊካኖች እና ሰባት ዴሞክራቶች እንዲጠየቅ ደግፈዋል።

የኮሚቴው ምክትል ሊቀመንበር ሊዝ ቼኒ በመክፈቻ ንግግራቸው ባነን ታህሳስ 28 ለተካሄደው ተቃውሞ እና የትራምፕን የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤቱን ለማጣጣል ስለማሰባቸው ቀደም ያለ መረጃ ነበራቸው ሲሉ ተናግረዋል።

የ 67 ዓመቱ ባነን እአአ በ2017 ከኋይት ሃውስ ተባረዋል። የካፒቶል ሂል ሁከት በተነሳበት ጊዜ በመንግስት ሥራ ላይ አልነበሩም።

ትራምፕ የቀድሞው ረዳቶች መረጃን ለመከልከል ባላቸው መብትን ምክንያት የምክር ቤቱን ኮሚቴ ጥያቄዎች ውድቅ እንዲያደርግ አሳስበዋል።

በአብዛኛው ሠላማዊ በነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ወቅት የትራምፕ ደጋፊዎች ባይደን አሸነፉ የሚለውን የምርጫ የምስክር ወረቀት ለማደናቀፍ የካፒቶልን ህንፃን መውረራቸው ይታወሳል።

ከ670 በላይ ሰዎች በግርግሩ ተሳትፈዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

መረጃዎች ባነንን ጠቅሰው እንደሚያሳዩት በረብሻው ዋዜማ ላይ ረብሻ እንደሚቀሰቀስ ቀድመው ተናግሮ ነበር።

ባነን በተደጋጋሚ ከኮሚቴው ፊት የመቅረብ ዕቅድ እንደሌለው ተናግሯል።

ዲሞክራቶች ባንን የታችኛው ምክር ቤት ያለውን የኃይል ሚዛን ሊለውጥ እስከሚችልበት የህዳር 2022 ምርጫ ድረስ ሂደቱን ወደ ኋላ ለመግፋት ይጥራል ብለው ይከራከራሉ።