ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰለሞን ባረጋ በቶኪዮ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኘ
ኢትዮጵያዊ አትሌት ሰለሞን ባረጋ በጃፓን ቶኪዮ ኦሎምፒክ በ10 ሺህ ሜትር በማሸነፍ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝቷል።
አትሌቱ በሩጫው ድንቅ ችሎታ ያሳየ ሲሆን በተለይም በመጨረሻው ዙር ባሳየው ብቃትና ፍጥነት አትሌቶቹ ሊደርሱበት አልቻሉም።
ሰለሞን በዚህ ውድድር ያስመዘገበው ሰዓት 27፡43፡22 ሲሆን የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነውንም ጆሹዋ ቼፕቴጊን አስከትሎ ነው የገባው።
የ21 አመቱ ሰለሞን ውድድሩን ማሸነፉ በስፍራው የነበሩ ኢትዮጵያውያንን በከፍተኛ ሁኔታም እንዳስደሰተ ተዘግቧል።
በርካቶችም ሲደንሱና ሲጨፍሩም ታይተዋል።
ድሉንም አስመልክቶ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን የማህበራዊ ትስስር ገፅ ላይ እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
"ለመላው የሃገራችንን ህዝቦች በራሴና በኢትዮጵያ አትሌቲክሰ ፌደረሽን ስራ አስፈፃሚና ማኔጅመንት ኮሚቴ፣ አሰልጣኞች፣ ኦፊሻሎችና ሰራተኞች ስም በድጋሚ እንኳን ደስ አለን እያልኩኝ ላለፉት ስምንት የዝግጅት ወራት ከጎናችን ለነበራችሁ በሙሉ ምስጋናዬ የላቀ ነው ድሉ ይቀጥላል፡፡" ብለዋል።
በዚህ ውድድር ላይ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷቸው የነበሩት የኡጋንዳ አትሌቶች ጆሹዋ ቼፕቴጌይ ብር ሲወስድ ሌላኛው ኡጋንዳዊ ጃኮብ ኪፕሊሞ ነሐስ ሜዳልያ በማሰነፍ ተከታትለው ገብተዋል።
በዚህ ውድድር ላይ አትሌት በሪሁ አረጋዊ 4ኛ እንዲሁም አትሌት ዮሚፍ ቀጄልቻ ስምንተኛ ስፍራ አግኝተዋል።