ተመድ በትግራይ ያሉ ስደተኞችን የተመለከቱ ሪፖርቶች አሳሳቢ መሆናቸውን ገለፀ

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ኤጄንሲ በትግራይ ክልል የሚገኙ ኤርትራዊያን ስደተኞች ላይ ደርሰዋል የተባሉ የጥቃት ሪፖርቶች እንዳሳሰቡት ገለጸ።

የኤጀንሲው የኢትዯጰያ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ እንዳስታወቁት በምዕራባዊው የሽረ ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኤርትራዊያን ስደተኞች ተገድለዋል የሚሉ ሪፖርቶችን "በኦንላይን እና ከሌሎች ምንጮች" መረዳታታቸውን አስታውቀዋል፡፡

«እነዚህን ዘገባዎች በአንክሮ የምንመለከታቸው ሲሆን ሪፖርቶቹን እንደሰማንም ወዲያውኑ በሽረ የሚገኙ ሠራተኞቻችንን ፣ አጋሮቻችንን እና ኤርትራውያን ስደተኞችን ለማግኘት ሞክረናል» ሲሉ ኔቨን ክሬቨንኮቪክ ለቢቢሲ በኢሜይል ገልጸዋል።

«እስካሁን እየደረሱን ያሉ ማናቸውንም ክሶች ማረጋገጥ ባንችልም የዘገባዎቹን ትክክለኛነት ለመገምገም የሚረዱ ተገቢ መረጃዎችን መሰብሰባችንን እንቀጥላለን» ሲሉ ቃል አቀባዩ አክለዋል።

የመብት ተሟጋቾች በርካታ ኤርትራዊያን ስደተኞች በአካባቢው ባሉ ሚሊሻዎች በጭካኔ መገደላቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች ደርሰውናል ሲሉ እየገለጹ ይገኛሉ።

ባለፈው ሳምንት የመከላከያ ሰራዊት ትግራይን ለቆ መውጣቱን ተከትሎ በክልሉ ሁሉም የግንኙነት አማራጮች መጥፋት ሪፖርቶቹን ለማረጋገጥ ከባድ አድርጎታል።

የመጠለያ ጣቢያዎችን ደህንነት የማረጋገጥ ተቀዳሚ ኃላፊነት ከመንግስት ባለስልጣናት የሚጠበቅ ሲሆን ከአከባቢው ካሉ አስተዳዳሪዎች ብሎም ከኢትዮጵያ የስደተኞች ኤጄንሲ ጋር በመተባበር በካምፖቹ ውስጥ ያሉ ስደተኞችን ደህንነትና ጥበቃን ማረጋገጥ እንደሚቀጥል ኤጅንሲው ለቢቢሲ ገልጿል።

ሆኖም የፌደራል ባለስልጣናት በትግራይ ክልል ያለውን የሲቪል እና የወታራዊ ሃይል ማስወጣቱን ተከትሎ የስደተኞችን ደህንነት እንዴት ማረጋገጥ እንደሚችል ግልፅ አይደለም።

በህዳር መጀመሪያ በትግራይ ክልል ጦርነቱ ከመቀስቀሱ በፊት 100,ሺህ የሚጠጉ ኤርትራዊያን በስደተኞች በክልሉ ባሉ ካምፖች ውስጥ ነበሩ።

በጦርነቱ መቀስቀስም ከአራቱ ካምፖች መካከል ሁለቱ በኋላ መውደማቸው የታወቀ ሲሆን በካምፖቹ ተጠልለው ከነበሩት ከ 20 ሺ በላይ ስደተኞች መካከል ብዙዎቹ እስካሁን ያሉበት የሚታወቅ አይደለም፡፡

ምንም እንኳን የኤርትራ መንግስት ክሶቹን ቢያስተባብልም በርካታ ስደተኞች በኤርትራ መንግስት ታፍነው ተወስደዋል የሚሉ ክሶች ተደምጠዋል።

ከኤርትራ ድንበር ብዙም ሳይርቅ ተገንብተው የነበሩት የሽመልባ እና የህጻጽ ካምፖች ውስጥ ይገኙ የነበሩ የረድኤት ሰራተኞች ካምፖቹን ለቀው ሲወጡ ስደተኞቹ ለወራት ያህል ያለ ምግብ እና ሌሎች ወሳኝ አቅርቦቶች በከፍተና እንግልት ውስጥ ቆይተው ነበር።

የተወሰኑት ስደተኞች በትግራይ ክልል ደቡብ ምዕራባዊ ክፍል ወደሚገኙ እና በአንጻራዊነት ደህንነታቸው ወደተጠበቁ መጠለያ ካምፖች መሄድ ችለው ነበር።

በአጎራባች የአማራ ክልል አዲስ መጠለያ ክምፕ ለመገንባትም መሬት መመደቡን የመድ የስደተኞች ኤጀንሲው ተናግሯል።

በኢትዮጵያ ባጠቃላይ ወደ 200 ሺህ የሚጠጉ ኤርትራዊያን ስደተኞች እንዳሉ የመንግስት መግለጫዎች ያመለክታሉ ፡፡