ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በትግራይ 400ሺህ ሰዎች ተርበዋል ሲል ተመድ አስጠነቀቀ
በትግራይ ክልል የተከሰተው ግጭት ከ400 ሺህ በላይ ዜጎችን እየጎዳ ያለ ረሃብ አስከትሏል ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት ባለስልጣናት ገለጹ።
የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ቀውሱን አስመልክቶ ትናንት ምሽት ለመጀመሪያ ጊዜ ባደረጉት ይፋዊ ስብሰባ ወደ 33 ሺህ የሚጠጉ ህፃናት ከፍተኛ የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው አመላክተዋል።
ለስምንት ወራት የቆየውን ግጭት ተከትሎ ተጨማሪ 1.8 ሚሊዮን ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
የተናጥል የተኩስ አቁም ቢታወጅም ተጨማሪ ግጭቶች ሊከሰቱ ይችላሉ ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
ከህወሓት ኃይሎች ጋር ሲዋጋ የቆየው የፌደራሉ መንግሥት በአስቸኳይ ተፈጻሚ የሚሆን የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁ ይታወሳል።
የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው "ጠላቶቻቸውን" ከክልሉ ለማባረር ቃል ገብተዋል። በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች ከድርጊታቸው እዲቆጠቡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግፊት እየተደረገ ቢሆንም አልፎ አልፎ ግጭቶች መኖራቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
በትግራይ ኃይሎች እና በፌደራሉ መንግሥት መካከል የተካሄደው ውጊያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል።
በግጭቱ እየተሳተፉ ያሉት ሁሉም ወገኖች በጅምላ ግድያ እና በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይከሰሳሉ።
አርብ ዕለት በሺህዎች የሚቆጠሩ የተማረኩ የኢትዮጵያ ወታደሮች በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ጎዳናዎች ላይ መታየታቸውን ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል።
የተባበሩት መንግሥታት ተጠባባቂ የሰብዓዊ እርዳታ ኃላፊ በኒው ዮርክ በተደረገው ስብሰባ ለፀጥታው ምክር ቤት አባላት ባለፉት ሳምንታት በትግራይ ያለው ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ገልጸዋል።
ክልሉ "በአስር ዓመታት ውስጥ ከታየው እጅግ የከፋ የረሃብ ሁኔታ" እያጋጠመው መሆኑን ራምሽ ራጅሲንግሃም ተናግረዋል።
አክለውም አብዛኛዎቹም ሴቶች እና ህጻናት የሆኑ ወደ 5.2 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ አሁንም ሰብዓዊ ድጋፍ ይፈልጋል ብለዋል።
የትግራይ አማጽያን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ አብዛኛውን የሰሜን አካባቢዎች ከተቆጣጠሩ በኋላ እርዳታ እንዳይደርስ አግዷል በሚል የሚቀርብበትን ክስ የኢትዮጵያ መንግሥት አስተባብሏል።