የትግራይ ፖለቲካዊ ዑደትና አሁን ያለው ሁኔታ ሲቃኝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፉት ዓመታት ኢትዮጵያ የዓለም አቀፉ ዜና ዋና አርእስት ሆና ቆየች። ያለ ምክንያት አይደለም።
በአንድ በኩል ምጣኔ ሀብቷ እየተመነደገ ነበር። በሌላ በኩል የፖለቲካ ሥርዓቷ መልክ እየያዘ ይመስል ነበር።
ይህ በጎ ምሥል ምዕራባዊያን ስለኢትዮጵያ ለዓመታት ያውቁት ከነበረው አሉታዊ ምሥል ፍጹም ተቃራኒው ነበር።
ኢትዮጵያ በዓለም እጅግ ድሀ ከሚባሉ አገራት ተርታ ስሟ የሚነሳ አገር ነበረች።
አሁን ደግሞ ነገሮች ተመልሰው እየተቀየሩ ይመስላል።
በሰሜን ኢትዮጵያ አሁን ወታደራዊ ግጭት እና ሰብአዊ ቀውስ ተከስቷል።
ነገሩ ወደየት እንደሚያመራ አይታወቅም። ምናልባት የአገሪቱን መጻኢ ዕድል የሚወስን ይሆናል። ዳፋው ለጎረቤት አገራትም ሊተርፍ ይችል ይሆናል።
ከሰሞኑ አማጺው የትግራይ ኃይል የክልሉን ዋና ከተማ መቀለን መልሶ ተቆጣጥሯል። ዋና ከተማዋ ከኅዳር ወዲህ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነበረች።
አሁን እዚያ ምን እየሆነ እንዳለና አገሪቱ እዚህ እንዴት እንደደረሰች በአጭሩ እንቃኝ።
በትግራይ እየሆነ ያለው ምንድነው?
በትግራይ ወታደራዊ ፍጥጫ አዲስ ነገር አይደለም።
በትግራይ 7 ሚሊዮን ሕዝብ ይኖራል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር 122 ሚሊዮን ደርሷል። ትግራዋያን ከኦሮሞና ከአማራ ቀጥሎ በአገሪቱ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ካላቸው ሕዝቦች መካከል የሚገኙ ናቸው።
ይህ ክልል ከማዕከላዊ መንግሥቱ ጋር ከፍተኛ ቅራኔ ውስጥ የገባ ነው። ታዲያ ይህ በታሪክ አሁን ብቻ የሆነ አይደለም።
የንጉሡ መገርሰስን ተከትሎ በመጣው ወታደራዊ አስተዳደር (ደርግ) ጊዜም የነበረ ስሜት ነው። ረዥሙ ጊዜ በእርስ በእርስ ጦርነት የጠፋበት ወቅት ነው።
ትግራይ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከ1983 እስከ 1985 የነበረው ድርቅና ረሀብ ከተከሰተባቸው ቦታዎች ዋንኛዋ ናት።
በዚህ ረሀብ ከአንድ ሚሊዮን ዜጎች በላይ መሞታቸው ይገመታል። ረሀቡ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ደግሞ ከቀዬዎቻቸው ያፈናቀለ ነበር።
ይህ ቀድሞ የነበረ ታሪክ ነው። ከዚያ በኋላ ሁኔዎች ተቀይረዋል።
ለአስርታት የጸና አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት በክልሉ ከመጣ በኋላ በጥቅምት 2013 ዓ.ም አዲስ ጦርነት አገረሸ። ይህም በማዕከላዊ መንግሥትና ክልሉን በሚያስተዳድረው ኃይል መካከል የተከሰተ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጦርነቱ እንዴትና ለምን ተጀመረ?
ህወሓት የደርግ ሥርዓትን ከገረሰሰ በኋላ ኢህአዴግ በሚባለው ግንባር አውራው ፓርቲ ሆነ።
ህወሓት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መዋቅር ለአስርታት ሁነኛው ኃይል ሆኖ ቆይቷል። ይህም እስከ 2010 የቀጠለ ነበር።
በዚህ ዓመት የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ብቅ አሉ። አዲስ የፖለቲካ ውህድ ፓርቲን መሠረቱ። ህወሓት በዚህ ጥምር ፓርቲ ውስጥ አልሳተፍም አለ።
ያም ሆኖ ህወሓት በትግራይ በሥልጣን ላይ ነበር። ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ የዐቢይ አህመድን አስተዳደር ገሸሽ በማድረግ ክልላዊ ምርጫን አደረገ።
በዚህ ወቅት ማዕከላዊው መንግሥት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የተነሳ ምርጫ እንዲራዘም ወስኖ ነበር።
ከሁለት ወራት በኋላ የህወሓት ኃይል በትግራይ በነበሩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የጦር ሰፈር ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሰነዘረ።
ይህን ተከትሎ የማዕከላዊው መንግሥት ወታደራዊ ዘመቻን ከፈተ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደረሰው ጉዳት ምን ያህል ነው?
ማዕከላዊው መንግሥት በትግራይ ስለሆነው ነገር ጋዜጠኞች ሙሉ መረጃ እንዲደርሳቸው፣ መረጃ እንደልብ እንዲያገኙ አድርጓል ለማለት አያስደፍርም።
ሆኖም ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈና ሚሊዮኖችን እንዳፈናቀለ እሙን ነው።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በክልሉ ከአምስት ሚሊዮን ሰዎች በላይ አስቸኳይ እርዳታ ያሻቸዋል። ከ350ሺህ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለከፍተኛ ረሀብ/ቸነፈር የተጋለጡ ናቸው።
የትግራይ ሁኔታ በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ተጽእኖ የሚኖረው እንዴት ነው?
በትግራይ የተከሰተው ፖለቲካዊና ወታደራዊ ቀውስ እዚያው የሚያበቃ አይደለም። ዳፋው ለጎረቤት አገራትም የሚተርፍ ነው።
በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን መሰደዳቸውን ልብ ይሏል።
የኤርትራ ወታደሮች በህወሓት ወታደሮች ላይ ጦርነት ከፍተው በነገሩ እጃቸውን አስገብተዋል። አሁን የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ያሉበት ሁኔታ ግን ግልጽ አይደለም።
የማዕከላዊው መንግሥት በትግራይ ጦርነት በመጠመዱ በሶማሊያ አልሸባብን ለመቆጣጠር ያደርግ በነበረው ጥረት ላይ ተጽእኖ እንደሚያሳድርበት ይገመታል።
"ይህ ጦርነት ከባቢያዊ ነው" ይላል የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ ራሺድ አብዲ።
አብዲን የመሰሉ ተንታኞች እንደሚሉት ጦርነቱ ኢትዮጵያን ማዳከም ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው አገራት ቀውስም ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ለምሳሌ ጦርነቱ በኢትዮጵያ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች በማዕከላዊው መንግሥቱ ላይ እንዲያምጹ ሊያነሳሳቸው ይችላል።
ይህ የትግራይ ጦርነት በተጀመረ ማግስት የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስ "የኢትዮጵያ መረጋጋት ለአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ቁልፍ ነው" ሲሉ ተናግረው ነበር።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምን ይላል?
የዩናይትድ ኪንግደም፣ የአሜሪካ እና አየርላንድ መንግሥታት በጋራ የጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ ጠይቀዋል።
አንቶኒዮ ጉቴሬስ ሰኞ ዕለት ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ስልክ እንደደወሉ እና የተኩስ አቁም እንደሚደረግ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ እስከ አሁን ድረስ የዲፕሎማሲ ጣልቃ ገብነትን ሲቃወም ቆይቷል።
ከዚያ ይልቅ ነገሩ የውስጥ ጉዳይ እንደሆነና ችግሩ በአጭር ጊዜ ሊፈታ እንደሚችል የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማሳመን ሲተጋ ነበር።
ማዕከላዊ መንግሥቱ ይህን ጦርነት "ሕግ የማስከበር ዘመቻ" ሲል ነው የሚጠራው። ዘመቻው ሕገ መንግሥቱን ለመጣስ በሚሞክር አንድ ቡድን ስብስብ ላይ የተቃጣ እንደሆነ ይናገራል።













