ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፈቱላህ ጉለን የወንድም ልጅ ከናይሮቢ ጎዳና ታፍኖ ወደ ቱርክ መወሰዱ ተነገረ
የሃይማኖት መምህሩ ፈቱላህ ጉለን የወንድም ልጅ በቱርክ የደኅንነት አባላት ተይዞ ወደ ቱርክ መወሰዱን የቱርክ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
ሰልሀዲን ጉለን በአጎቱ የሚመራውና በቱርክ ሕገ ወጥ የተባለው ስብስብ አባል በመሆኑ ነው የተያዘው። አሁን የት እንደሚገኝ ግን አልተገለጸም።
ኬንያ ውስጥ የምታስተምረው ባለቤቱ፤ ከግንቦት መጀመሪያ አንስቶ ጠፍቶ እንደነበር እና ከናይሮቢ ታፍኖ ስለመወሰዱ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በለቀቀችው ቪድዮ አስታውቃለች።
ግለሰቡ ከኬንያ መዲና ታፍኖ ስለመወሰዱ ባለቤት ትናገር እንጂ አናዱሉ የዜና ወኪል ባወጣው ዘገባ ላይ የቱርክ ብሔራዊ ደኅንነት ተቋም (ኤምአይቲ) ሰልሀዲንን ያሰረው ከኬንያ መንግሥት ጋር ተስማምቶ ስለመሆኑ የተባለ ነገር የለም።
የቱርኩ አናዶሉ የዜና ወኪል ያተመው ፎቶ ሰልሀዲን በካቴና ታስሮ፣ በግራና በቀኙ የቱርክ ሰንደቅ አላማ ተሰቅሎ ያሳያል።
ከቱርክ የተሰደዱት ፈቱላህ ጉለን እአአ በ2016 የከሸፈውን መፈንቅለ መንግሥት በማቀናበር ተከሰዋል። በወቅቱ 251 ሰዎች ሲሞቱ 2,000 ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ሰልሀዲን እና አጎቱ በመፈንቅለ መንግሥቱ እጃችን የለበትም ብለዋል።
ፈቱላህ በተከታዮቻቸው ዘንድ መንፈሳዊ መሪ ተብለው ይጠራሉ። በቱርክ ሁለተኛው ኃያል ሰው ተብለውም ይጠራሉ።
ጉለን የተባለው ንቅናቄያቸው አሜሪካ ውስጥ ትምህርት ቤቶች እና የተራድኦ ድርጅቶችን ይዟል። እሳቸውም የሚኖሩት አሜሪካ ነው።
ቱርክ የጉለን ንቅናቄን የሽብር ተቋም ብላ ፈርጃለች።
ፈቱላህ ግን በቱርክ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እንዳልተሳተፉ ይናገራሉ። ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ወዲህ አሜሪካ በስደት እየኖሩ ሲሆን፤ አሜሪካ ፈቱላህን ለቱርክ አሳልፋ እንድትሰጥም ተጠይቋል።
የቱርኩ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን፤ ከፈቱላህ ጉለን ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ከ100,000 በላይ መምህራን፣ ዳኞችና የመንግሥት ሠራተኞችን አባረዋል።
ክስ ከተመሠረተባቸው መካከል 2,500 የሚጠጉት የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።
በአፍሪካ እና በባኪንስ የጉላህ ንቅናቄ አባል ናቸው የተባሉ ሰዎችንም ቱርክ በቁጥጥር ሥር አውላለች።
2018 ላይ ስድስት ቱርካውያን ኮሶቮ ውስጥ ከተያዙ በኋላ ፖለቲካዊ ቀውስ መቀስቀሱ አይዘነጋም። የኮሶቮ የውስጥ ጉዳይ ሚንስትር እና የደኅንነት ኃላፊ ከሥልጣናቸው ተነስተውም ነበር።