ዛምቢያ ለዕድሜ ልክ እስረኞች የሁለት ሳምንት ዕረፍት ፈቀደች

ዛምቢያ ለዕድሜ ልክ እስረኞች የሁለት ሳምንት ዕረፍት ፈቀደች

የፎቶው ባለመብት, AFP

በዛምቢያ የዕድሜ ልክ እስረኞች ተገምግመው "ጥሩ ሥነ ምግባር" ካሳዩ ቤተሰቦቻቸውን ለመጎብኘት የሁለት ሳምንት ዕረፍት ማግኘት ይጀምራሉ፡፡

በፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ በተፈረመው አዲስ ሕግ መሠረት ኅብረተሰቡ ላይ አደጋ አይፈጥሩም ተብለው የተመረጡት እስረኞች ፈቃድ ይሰጣቸዋል፡፡

እንደ ዛምቢያ ኮሚሽነር ጄነራል ቺሴላ ቼሌሼ ከሆነ መጸጸታቸውን የሚያሳዩ እና ከወንጀል የራቁ እስረኞች በአዲሱ ሕግ ይጠቀማሉ።

ፍርደኞቹ እነዚህ መብቶችን የሚያገኙት የዛምቢያ ማረሚያ አገልግሎት ለፕሬዝዳንት ሉንጉ በጽሑፍ ካሳወቃቸው ብቻ ነው ተብሏል።

"ወንጀል ከፈጸሙ ግን ፈቃዳቸው ይሰረዛል" ብለዋል፡፡

አያይዘውም "ኮሚሽን ጄኔራሉ እስረኞች የግል ወይም የቤተሰብ ጉዳዮችን እንዲታደሙ ፈቃድ የመስጠት መብት ያለው ሲሆን፤ ጊዜው በተለያዩ ሁኔታዎች በጄኔራል ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት የሚወሰን እና የሚሰጥ ነው" ሲሉ አክለዋል።

አንዳንድ የዛምቢያ ዜጎች በትዊተር ገጻቸው አዲሱን ሕግ ለወንጀለኞች "የፌሽታ ቀን" ሲሉ ሰይመውታል፡፡