ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቻድ ወታደራዊ መንግሥት አማጺያንን ድል አደረኩ አለ
የቻድ ወታደራዊ መንግሥት ለሳምንታት ከቆየ ውጊያ በኋላ በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል የተነሱትን አማጺያን ድል ማድረጉን አስታወቀ።
መንግሥቱ ድል አድርጌያቸዋለሁ ያለው አማጺያን ግን እንደውም ውጊያው አልቆመም ብለዋል።
የአገሪቱ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኢድሪስ ዴቢ ባሳለፍነው ወር መቀመጫቸውን ሊቢያ ካደረጉት አማጺያን በተተኮሰባቸው ጥይት ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ አገሪቱ ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ገብታ ነበር።
የፕሬዝዳንቱን ሞት ተከትሎም ወንድ ልጃቸው ወታደራዊ መንግሥቱን መምራት የጀመረ ሲሆን በርካታ አገራት፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችና የሲቪል ማህበረሰብ አባላት ተቃውሟቸውን ሲገልጹ ነበር። ዜጎችም አደባባይ በመውጣት የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ጠይቀዋል።
መንግሥት አማጺያኑን ድል አድርጊያለሁ ማለቱን ተከትሎ ትናንት እሁድ ዜጎች በመዲናዋ ጎዳናዎች ላይ ደስታቸውን ሲገልጹ ነበር። ይህ ድልም ለወታደራዊው መንግሥቱ በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነቱን እንደሚጨምረው ይጠበቃል።
አንዳንድ ዜጎች እንደመውም ከግዳጅ የሚመለሱ እና ወታደራዊ ትዕይንት አሳይተው የሚያሳዩ ወታደሮችን መንገድ ላይ በመጠበቅ ደስታቸውን እና አድናቆታቸውን ሲገልጹላቸው ነበር።
በአንድ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ደግሞ በመንግሥት ወታደሮች የተማረኩ ናቸው የተባሉ አማጺያንን ጋዜጠኞች እንዲያዩዋቸው ተደርጓል።
ቻድ ከፍተኛ ወታደራዊ ስልጠና የወሰዱና እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቁ ወታደሮች ካሏቸው የምዕራብ አፍሪካ አገራት መካከል አንደኛዋ ስትሆን በሳህል ግዛት የሚንቀሳቀሱ ኢስላማዊ አክራሪዎችን ለመዋጋት ደግሞ የጂ5 አገራት ቀላል የማይባል ወታደራዊ ድጋፍ ያደርጉላታል።
በዋና ከተማዋ በሚገኘው የወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉ አማጺያን ከነመሳሪያቸው በክፍት መኪና ላይ ተጭነውና እጃቸው በካቴና ታስሮ ጋዜጠኞች እንዲያዩዋቸው ተደርጓል።
የአማጺ ቡድኑ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ የ30 ዓመታት ስልጣን ላይ መቆየት በመቃወም ባሳለፍነው ወር ነበር ከሊቢያ ወደ ቻድ ድንበር አቋርጦ የገባው።
በአሁኑ ሰዓት አማጺያኑ ለወታደራዊው መንግሥት ስጋት መፍጠር በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ይሁኑ አይሁኑ የታወቀ ነገር ባይኖርም፤ ሬውተርስ ዜና ወኪል ግን አማጺያኑ ውጊያው ገና አላለቀም ስለማለታቸው ዘግቧል።
በቅርብ ሳምንታት ወታደራዊው መንግሥት ወርዶ የሲቪል መንግሥት ይቋቋም የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው ጉዳት ደርሶ ነበር።