የጥበብ ስራው የተበላሸው ዛምቢያዊ ቀራፂ በረሃብ አድማ ላይ ነው ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Alexis Phiri
የዛምቢያው አርቲስት የእንስሳትን አደንና የአካባቢ ብክለት ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር የሰራው ቅርፅ በመንገድ ስራ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ መሆኑን ተከትሎ ተቃውሞውን ለመግለፅ የረሃብ አድማ ላይ ነው ተብሏል።
ካቼሬ የተባለ የጥበብ ስቱዲዮ አስተባባሪ የሆነው ቀራፂው አሌክስ ፊሪ ከሌሎች አርቲስቶች ጋር በመሆን ነበር ከዘጠኝ አመት በፊት በመዲናዋ ሉሳካ ትልቅ የአውራሪስ ቅርፅ ያቆሙት።
ቅርፁ የተሰራው ከፕላስቲክ ሲሆን ይህም በአካካቢው ላይ የሚያመጡትን ብክለት ለነዋሪው ለማስታወስ ነው ተብሏል።
በመዲናዋ ሉሳካ የመንገድ ማስፋት ፕሮጀክት ጋር ተያይዞ ቅርፁ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ነው ተብሏል።
"በእንዲህ አይነት ሁኔታ ስንት የለፋንበት የአውራሪስ ቅርፅ ከጥቅም ውጭ መሆኑ ያሳዝናል። እንደ ጥበብ ሰራ ሳይሆን እንደማይጠቅምና እንደማይረባ ነገር ነው የተቆጠረው" በማለት አርቲስቱ ለቢቢሲ ተናግሯል።
"የጥበብ ስራ በገንዘብ አይገመትም። አካባቢያችን ላይ የሚደርሰውን ብክለትና በእልቂት ላይ ያሉ እንስሶችን ደህንነት ለመታደግ ያለመውን ይህንን የጥበብ ሰራ ላይ ያደረሳችሁትን ጉዳት እንድታዩ እፈልጋለሁ" ብሏል።
አርቲስቱ የረሃብ አድማውን እያደረገ ያለው ተቃውሞውን ለማሰማት እንደሆነ አስታውሶ በዛሬው ዕለት ሙሉ ቀን እንደሚቀጥልም አስታውቋል።
"በዋነኝነት የጥበብ ስራው ከጥቅም ውጭ በመሆኑ የተሰማኝን ብስጭትና ተቃውሞ ለመግለፅ ቢሆንም የወደፊቱ ትውልድ የአካባቢያችንን ከብክለት መታደግና በአደጋ ላይ ያሉ ብርቅዬ እንስሳትን ለመጠበቅም ማስታወሻ ይሆናል" በማለት ለቢቢሲ ተናግሯል።












