የዓለም ንግድ ድርጅት ቀጣይ መሪ ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁት ናይጄሪያዊት

የጆ ባይደን አስተዳደር ቀጣዩ የዓለም ንግድ ድርጅት መሪ ማን ይሁን ለሚለው አጣብቂኝ ምላሽ መስጠቱ ተሰምቷል።

የጆ ባይደን አስተዳደር ለቀድሞዋ የናይጄሪያ ፋይናንስ ሚኒስትር ድጋፉን በመግለጽ ለረዥም ወራት ምላሽ ያላገኘውን ፉክክር መቋጫ አበጅቶለታል።

ንጎዚ ኦኮንጆ ኢዌላ ፕሬዝዳነት ትራምፕ ስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት የዓለም ንግድ ድርጅትን ለመምራት በሚደረገው ፉክክር ወቅት ከደቡብ ኮሪያዋ፣ ዩ ሚዩንግ ሂ ጋር ብርቱ ተፎካካሪ ነበሩ።

ወይዘሪት ዮ ከተፎካካሪነታቸው ራሳቸውን አግልለዋል።

የናይጄሪያ የቀድሞ ፋይናንስ ሚኒስትር የነበሩት ሴት የዓለም ንግድ ድርጅትን እንዲመሩ መመረጣቸው ይፋ ከሆነ ዶ/ር ኦኮንጆ ኢዌላ የዓለም ንግድ ድርጅት መሪ በመሆን የመጀመሪያዋ ሴት እና አፍሪካዊት ይሆናሉ ማለት ነው።

ዶ/ር ኦኮንጆ ኢዌላ አርብ ዕለት ተፎካካሪያቸው የነበሩትን ደቡብ ኮሪያዊት አንቆለጳጵሰው "አብረን የምንሠራቸው ቁልፍ ሥራዎች ከፊታችን ይጠብቁናል" ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያቸው ላይ አስፍረዋል።

የዓለም ንግድ ድርጅት አስመራጭ ኮሚቴ በጥቅምት ወር ለ164 አባላቱ ዶ/ር ኦኮንጆ ኢዌላን በተሰናባቹ ሮቤርቶ አዝቬዶ ምትክ እንዲሾም ጠይቀው ነበር።

በወቅቱ ቃል አቀባይ የነበሩት ግለሰብ "ከአንዱ በስተቀር ሁሉም ሹመቱን አጽድቀውታል" ብለው ነበር።

ዓለም ንግድ ድርጅትን " አሳፈሪ" እና ለቻይና ያደላል ሲሉ የገለፁት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የደቡብ ኮርያ ንግድ ሚኒስትር የሆኑት ወይዘሪት ዮ ቦታውን እንዲያገኙ ፈልገው ነበር።

ወይዘሪት ዮ አርብ ዕለት ከተፎካካሪነት ራሳቸውን ሲያገሉ እንደተናገሩት እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ከአሜሪካ ጋር "በቅርበት በመመካከር" መሆኑን ገልፀዋል።

ዋይት ሐውስም ወይዘሪት ዮን ላደረጉት ጠንካራ የምረጡኝ ዘመቻ አመስግኗል።

አሜሪካም ሆኑ ደቡብ ኮሪያ ቀጣዩ የዓለም ንግድ ድርጅት ኃላፊ ማን መሆን እንዳለበት በሚወሰነው ውሳኔ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።