አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ የደህንነት ስጋት አለን በሚል ከፍርድ ቤት ቀሩ

በሽብር ወንጀል ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ የደህንነት ስጋት አለን በሚል ምክንያት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀሩ።

የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት የተከሳሾች የንብረት እግድ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ነበር ለዛሬ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረው። ይሁን እንጂ ከተከሳሾች መካከል አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ፍርድ ቤት አልተገኙም።

ፍርድ ቤቱም አቶ ጀዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ለምን ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ በጠየቀበት ወቅት፤ የማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ተከሳሾቹ የደህንነት ስጋት አለብን በሚል ምክንያት አለመቅረታቸውን ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል።

በእነ አቶ ጀዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ውስጥ የተከሰሱት አቶ ሐምዛ ቦረና፤ "አቶ ጀዋር እና አቶ በቀለ 'አገሪቱ አሁን ያለችበት ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ከፍተኛ ስጋት ስላለን በዚህ ቀጠሮ መገኘት አንችልም' ብለዋል" ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

"አሁን ባለው ሁኔታ አይደለም ጉዳት ይቅርና ሙከራ [የግድያ] ቢደረግብን አገሪቱ ወደ ከፋ አደጋ ውስጥ ስለሚያስገባት ለአገሪቱ በማሰብ ወደ ፍርድ ቤት ከሚደረግ ጉዞ እራሳችንን ቆጥበናል" ስለማለታቸው አቶ ሐምዛ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አሁን አገሪቱ ውጥረት ውስጥ እያለች በንብረት ጉዳይ ላይ ለመከራከር ፍርድ ቤት መመላለስ 'ለእኛ ሃፍረት' ነው በሚል ምክንያት ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን አቶ ሐምዛ፤ አቶ ጀዋር እና አቶ በቀለን ወክለው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

በእነ አቶ ጀዋር መዝገብ ስር ተከሰው ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡ ተከሳሾችም አገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ አሳስቦናል በማለት ለፍርድ ቤቱ መናገራቸውን ከእነ አቶ ጀዋር ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ከድር ቡሎ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ በንብረት እግዱ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለሕዳር 15 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል።