ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በተከሰተው አለመረጋጋት ለወደሙ ኢንቨስትመንቶች መንግሥት የሚከፍለው ካሳ እንደሌለ ተገለፀ
የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተ አለመረጋጋት ለወደሙ ኢንቨስትመንቶች የሚከፍለው ካሳ አለመኖሩን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ።
የድምጻዊ ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች 89 የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ አልያም በከፊል መውደማቸው ኮሚሽኑ ለቢቢሲ ገልጿል።
ከወራት በፊት በክልሉ በተስተዋለው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ከተሞች መካከል ሻሸመኔ ፤ ዝዋይ የሚገኙበት ሲሆን የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ደርሷል።
የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዋሲሁን ጎልጋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የአርቲስት ሃጫሉን ግድያን ተከትሎ በኢንቨስትመንት ድርጅቶች ላይ የደረሰው ጉዳት በገንዘብ ሲሰላ ከ3 ቢሊዮን በር በላይ እንደሚሆን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኮሚሽኑ ጉዳቱ ከደረሰ በኋላ የተለያዩ ድርጅቶችን ለማገዝ የተለያዩ እርምጃዎች መውሰዱንም ገልፀዋል።
"የደረሰው ጉዳት ከተለየ በኋላ ከፌደራል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር በመወያየት ከዚህ በፊት መኪና እና ማሽኖችን ከቀረጥ ነጻ ያስገቡ አሁንም በድጋሚ በነጻ እንዲያስገቡ፣ የባንክ ብድር ያለባቸው ደግሞ የእፎይታ ጊዜ እንዲሰጣቸው ተወስኗል" ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸው እነዚህ የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ከዚህ በፊት የመሬት ጥያቄ አቅርበው ከነበረ በፍጥነት ምላሽ እንዲያገኙ መወሰኑን ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል።
እነዚህ ድርጅቶች ከጉዳታቸው አገግመው ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ከማገዝ ውጪ ለደረሰው ጉዳት መንግሥት የሚከፍለው ምንም ዓይነት ካሳ እንደሌለ፣ እንዲሁም ለመክፈል ቃል የሚገባው ነገር አለመኖሩን አቶ ዋሲሁን ገልፀዋል።
በአሁኑ ሰዓትም ጉዳት ከደረሰባቸው 89 ድርጅቶች መካከል ጥቂቶቹ ወደ ሥራ እየተመለሱ መሆኑን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ጊዜያት በሚፈጠረው አለመረጋጋት የተነሳ፣ በኢንቨስትመንት ድርጅቶች ላይ በሚደርሰው ጉዳት ሥራ ላይ ያሉ ኢንቨስትመንቶች በሙሉ አቅማቸው እንዳይሰሩ ጫና እያሳደረባቸው እንደሆነም ገልፀዋል።
" ኢንቨስትመንት የተረጋጋ ሰላም ይፈልጋል። የሰላም ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች ኢንቨስተሮች በሙሉ አቅማቸው ለመስራት ስጋት ያድርባቸዋል። ይህም አንድ ጫና ነው፤ በቅርቡ የደረሰው አለመረጋጋትም እንደዚህ አይነት ጫና ፈጥሯል" ብለዋል።
ሥራ ላይ ተሰማርተው በሚገኙት ላይም ፍርሃት ቢታይም የኦሮሚያ ኢንቨስትመንት መስህብ ጭማሬ እያሳየ መሆኑንና ያለው ፍላጎትም ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከ12 ሺህ በላይ የኢንቨስትመሰንት ድርጅቶች ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።