ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቴክኖሎጂ፡ ቻይና አደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪዎችን ድሮን ተጠቅማ ያዘች
የቻይና ፖሊስ ሰው አልባ አነስተኛ አውሮፕላን (ድሮን) በመጠቀም አደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎች የንግድ ልውውጥ ለማድረግ ሲደራደሩ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል አግኝቷል። አዘዋዋሪዎቹን በቁጥጥር ስርም አውሏል።
በብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተንቀሳቃሽ ምስሉ ተሰራጭቷል።
አንዳንዶች ድሮን ሌሎች ወንጀሎችንም ለማጋለጥ መዋል አለበት ሲሉ፤ "ሚሥጥራዊነት ቀረ" ብለው ቅሬታ ያሰሙም ነበሩ።
የግላዊነት መብት ተሟጋቾች ዩናይትድ ኪንግደምና ሌሎችም የአውሮፓ አገራት የሚጠቀሟቸው የስለላ ቴክኖሎጂዎች ያሰጓቸዋል።
የቻይና ሚዲያ እንደዘገበው፤ ድሮኑ ፖሊሶችን በደቡባዊ ግዛት ወደሚገኝ የጡብ ፋብሪካ መርቷቸዋል። ግለሰቦቹ አደንዛዥ እጽ ሲለዋወጡ ነበርም ተብሏል።
ሂደቱን በቀጥታ ሲከታተሉ የነበሩ ሰዎች እጽ አዘዋዋሪዎቹን በቁጥጥር ስር አውለዋል።
'ቢግ ብራዘር ዋች' የተባለው ተቋም ኃላፊ ሲልኬ ካርሎ "የስለላ ቴክኖሎጂ አስጊነቱ እየጨመረ ነው። በተለይም ዩኬ እና ቻይና ዜጎቻቸውን እየተከታተሉ መሆኑ ያሳስባል" ብለዋል።
ኮቪድ-19 ከመጣ ወዲህ ኢንግላንድ ውስጥ በውበት ሳሎኖች ላይ በድሮን ስለላ ሲካሄድ እንደነበረ የጠቀሱት ኃላፊው "ምክር ቤት ፖሊሶች እንዴት ድሮንን መጠቀም እንዳለባቸው የሚደነግግ ሕግ ማውጣት አለበት" ብለዋል።
የእጽ አዘዋዋሪዎቹ ተንቀሳቃሽ ምስል ከተሰራጨ በኋላ፤ የቻይና ማኅበራዊ ሚዲያ ዌይቦ ተጠቃሚዎች አስተያየት እየተለዋወጡ ነው።
አንዳንዶች "እጽ አዘዋዋሪዎች በድሮን መገደል አለባቸው" ብለዋል።
በሌላ በኩል "የቻይና መንግሥት በሰማይ ላይም አይን አለው" በማለት ስለላው መባባሱን የተቹም አሉ።
አምና መስከረም ላይ ለ17 ዓመታት በሕግ ይፈለግ የነበረ ሰው በድሮን መያዙ ተገልጾ ነበር። ግለሰቡ ዋሻ ውስጥ ተደብቆ ነበር።
ኮቪድ-19ን ተከትሎ ድሮን በብዛት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ አደባባይ ላይ የተገኙ ሰዎችን በመቆጣት ለማሸማቀቅ ድሮን ጥቅም ላይ ውሏል።
ስፔንም እንቅስቃሴ ላይ የጣለችውን ገደብ ለማስተግበር ድሮን ተጠቅማለች።