ከክትባቱ በኋላ ወደ ቀድሞ ሕይወት ለመመለስ ምን ያህል ጊዜ ያስፈልጋል?

ይበለውና ለኮሮና የተሳካ ክትባት ቢገኝ በነገታው ዓለም ወደነበረችበት ትመለሳለች?

ሳይንቲስቶች ገና ምን ተይዞ? እያሉ ነው።

የሮያል ሶሳይቲ የሳይንቲስቶች ቡድን ባወጣው አንድ ጥናት የማይመስል ነገር ባንናገር ብሏል።

ክትባቱ ተገኝቶ እንኳን እቀባዎች መነሳት የሚገባቸው ቀስ በቀስ ነው። ምክንያቱም ክትባቱን ጀምሮ ለማዳረስ ቢያንስ ዓመት ካልሆነም ዓመታት ሊወስድ ይችላልና።

በአሁን ጊዜ ክትባት ፍለጋ በታሪክ ፈጣን የተባለ ርብርብ እየተካሄደ ነው። በመላው ዓለም በትንሹ 200 ክትባቶች በምርምር ላይ ናቸው።

ዶክተር ፊዮና ከሊ በኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን ነው የሚሰሩት። "ክትባት ትልቁ ተስፋችን ነው። ነገር ግን የክትባት ምርምር ሁልጊዜም በታሪክ እንደታየው እክል አያጣውም" ሲሉ ነገሩ አልጋ በአልጋ ሊሆን እንደማይችል ተናግረዋል።

በአሜሪካም ሆነ በብሪታኒያ ፍቱን ክትባት በዚህ ዓመት መጨረሻ ተገኝቶ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ክትባቱ ለዓለም እንደሚሰራጭ ትልቅ ተስፋ ተጥሏል።

ይህ ተስፋ ቀቢጸ ተስፋ ነው የሚለው የሮያል ሶሳይቲ ሪፖርት ነው።

ፍቱን ከትባት ተገኘ ማለት በአንድ ወር ውስጥ ሕዝቡ ሁሉ ይከተባል ማለት አይደለም። በትንሹ መንፈቅ፣ ካልሆነም ዓመትና ከዚያ በላይ ነው የሚሆነው። ይላሉ የጥናቱ አባል ፕሮፌሰር ሊላይ ሻህ።

በምንም ታሪክ ግን ሕይወት በፈረንጆች ፀደይ ወደ ቀድሞዋ ሁኔታ አትመለስም። ይላሉ።

አንዳንዶቹ የምርምር ሂደቶች አዲስ መንገድን የተከተሉ ከመሆናቸው የተነሳ በብዙ ቁጥር ተመርተው እንኳን አያውቁም። ከነዚህ መሀል አር ኤን ኤ ክትባቶች የሚባሉት ይጠቀሳሉ።

ለክትባቱም ሆነ ለምርቱ የሚሆኑ ግብአቶችና ጥሬ እቃዎች ውስብስብ ናቸው። ክትባቱን ወደ ተለያዩ ዓለማት ለማድረስ የሚፈልገው መሰረተ ልማትም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። አንዳንድ ክትባቶች ከዜሮ በታች እስከ 80 ሴንትግሬድ ቅዝቃዜን የሚፈልጉ ናቸው። ይህን የሚያሟላ ማቀዝቀዣ ለዓለም ማዳረስ ቀልድ አይደለም።

ፕሮፌ ሻህ እንደሚገምቱት በአንድ አገር ክትባቱን ለማድረስ ቢያንስ 30ሺ የሰለጠነ ሰራተኛ ይፈልጋል። ይህን ማሰልጠን በራሱ ጊዜ የሚፈልግ ነገር ነው።

አሁን ባለው ጥናት ውጤት መሰረት አንዳንድ የተሞከሩ ክትባቶች የበሽታ ተከላካይ ሴሎችን ምላሽ ማግኘት ያስቻሉ ሆነዋል። ነገር ግን ይህ በራሱ በቂ ነው ወይስ በሽታው በተከተበ ሰው ሊያገረሽ ይችላል የሚለው ገና ምላሽ ያላገኘ ጉዳይ ነው።

ከዚህ ሌላ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ።

የሚፈውስ ክትባት መቼ ይገኛል? ክትባቱ አስተማማኝ ነው ወይ? አስተማማኝ ከሆነስ በምን ፍጥነት ለዓለም ሕዝብ ይደርሳል የሚለው ሁሉ አልተመለሰም።

ሌላው ያልተመለሰው ጥያቄ ሰዎች ክትባቱን ቢወስዱ እንኳን አንድ ጊዜ የተወሰ ክትባት ለዘላለም ያገለግላል ወይስ በየሁለት ዓመቱ ድጋሚ መውሰድ ያስፈልጋል?

ፈዋሽ የተባለው ክትባት በረዥም ጊዜ የሚያመጣው የጎንዮሽ ጉዳትስ ቢኖር?

ክትባቱ አንድ ጠብታ መውሰድ በቂ ነው? ይህ የመጨረሻው ጥያቄ ብቻውን በቢሊዮን ሕዝቦች ሲሰላ የሚፈልገው ግብአትና መሰረተ ልማት እጥፍ ያደርገዋል።

ምናልባት ከዚህ ክትባት በኋላ አሁን ከምንይዘው ፓስፖርት ሌላ የክትባት ፓስፖርትን ያስገልገን ይሆናል። ከአገር አገር ለመንቀሳቀስ።

ዶ/ር አንድሩ ፕሪስተን በዩኒቨርሰቲ ኦፍ ባዝ ተመራማሪ ናቸው። ክትባቱ የሁሉም ነገር ቁልፍ አድርገው ሰዎች መመልከታቸው ትክክል አይደለም ይላሉ።

ምክንያቱም ብዙ ፈተናዎች ዓለማችን ይጠብቋታል። ክትባት ለመውሰድ ፍቃደኛ ያልሆኑ ሚሊዮኖች አሉ። እነሱስ ምንድነው የሚሆኑት የሚለው ሌላው ጥያቄ ነው።

አንድ ሰው አልከተብ ቢል የተከተበውን ይበክላል? አደጋስ አለው? ወይስ የራሱ ጉዳይ ተብሎ ይታለፋል? ማን ነው ተጠያቂው? ሕግስ ያስገድደዋል? እነዚህ ሁሉ ገና ያልተመለሱ ጥያቄዎች ናቸው።