ስሪ ላንካ ከዩኬ የተላከላትን ቆሻሻ መለሰች

ስሪ ላንካ 21 ኮንቴይነር ሙሉ ቆሻሻ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መለሰች።

ምክንያቱ ደግሞ የላክሽልኝ ቆሻሻ አደገኛ እና ለጤና ጠንቅ ስለሆነ ነው ብላታለች።

የስሪ ላንካ የጉምሩክ ኃላፊዎች እንደተናገሩት ከተላኩት 263 ኮንቴይነገሮች ውስጥ በብዙዎቹ ከሆስፒታል የወጡ ለጤና ጎጂ የሆኑ ቆሻሻዎች ተገኝተውባቸዋል።

ቆሻሻ የያዙ ኮንቴይነሮችን ወደ ስሪ ላንካ የሚያስመጣው አንድ የግል ድርጅት ነው።

ለወትሮ ከነዚህ ቆሻሻዎች በመልሶ ማደስ ሂደት ፍራሽ፣ ምንጣፍና የመሳሰሉት በስሪ ላንካ ይመረቱባቸው ነበር።

አሁንም ቢሆን ብዙዎቹ የቆሻሻ ኮንቴይነሮች በመጋዘን የሚገኙ ሲሆን እጅግ አደገኛ የሆኑት ብቻ ናቸው ወደ ዩኬ የተላኩት።

ወደ ስሪ ላንካ በተላከው የቆሻሻ ክምር ውስጥ የፕላስቲክና ላስቲክ ትራፊዎችም ተገኝተዋል።

21ዱ ኮንቴይነሮች ወደ ዩኬ የተመለሱት ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ነው።

የስሪ ላንካ ጉምሩክ ባለሥልጣን ቃል አቀባይ እንዳለው የተላኩት ቆሻሻዎች የአውሮጳ ኅብረትን ሕግና ደንብ የጣሱና ድርጊቱን ኃላፊነት የጎደለው ነው።

የእንግሊዝ የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ በበኩሉ ከስሪ ላንካ ተጨማሪ መረጃ ጠይቀናል ይህ እንዴት ሊፈጠር እንደቻለ ምርመራ እንጀምራለን ብሏል።

ብዙ የአካባቢው አገራት ከአውሮጳ የሚቀበሉትን ቆሻሻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየመለሱ ይገኛሉ።

ባለፈው ጥር ማሌዢያ 42 ሕገ-ወጥ የቆሻሻ ኮንቴይነሮችን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መመለሷ አይዘነጋም።