በናይጄሪያ በስርቆት የተጠረጠሩ የሆቴል ሰራተኞች እርቃን መጋለጥ ቁጣን ፈጠረ

በደቡባዊቷ ናይጄሪያ ዋሪ ግዛት የሚገኙ የሆቴል ሰራተኞች ሰርቃችኋል በሚል ልብሳቸውን ያስወለቋቸው አሰሪዎች ጉዳይ ቁጣን ቀስቅቀሷል።

የግዛቷ የሰብዓዊ መብት ጠበቆችም እንዲህ አዋርደው እርቃናቸውን ስላጋለጧቸው ካሳ ሊከፍሏቸው ይገባልም በሚል እየተሟገቲ ነው።

ምንም እንኳን ሰራተኞቹ ገንዘብ ሰርቀዋል በሚል ጠርጥረናቸው ነው ቢሉም የአገሪቱ ሚዲያ ግን ከእንግዶች የተሰጣቸው ጉርሻ (ቲፕ) ነው በማለት ዘግቧል።

በስርቆት ተጠረጠሩ የተባሉት አራት ሰራተኞች ሲሆኑ ከነዚህም መካከል ሶስቱ ሴቶች ናቸው። ልብሳቸውን እንዲያወልቁና ፓንት ብቻ እንዲያስቀሩ የተነገራቸው ሲሆን ፖሊስም በቦታው ላይ እንደነበረ ተገልጿል።

እርቃናቸውን የተጋለጡት የሆቴሉ ሰራተኞች ፎቶና ተንቀሳቃሽ ምስልም በማህበራዊ ሚዲያ በከፍተኛ ሁኔታ መጋራቱን ተከትሎም ነው በርካቶች የተቹት።

የሆቴሉ ባለቤት የአገሪቷ የቀድሞ ሚኒስትር እንደሆኑም ተገልጿል።

ጠበቆቹ ለሆቴሉ ባለቤት በላኩት ደብዳቤም የሰራተኞቹን ሰብዓዊ መብት በማዋረድና መሰረታዊ መብታቸውን በመጣስም ፍርድ ቤት እንደሚገትሯቸውም አሳውቀዋቸዋል።

ካሳና ይፋዊ የሆነ ይቅርታ እንዲጠይቁም በተጨማሪ ጠበቆቹ አሳስበዋል።

የጥቃቱ ሰለባዎች በበኩላቸው ፎቶዎችና ቪዲዮዎች በኢንተርኔት መለቀቃቸው ሆን ብሎ እነሱን ለማዋረድ የታቀደ ደባ ነው ብለዋል።