ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምጣኔ ሃብት ፡ አዲሶቹ የብር ኖቶች እና የያዟቸው የደኅንነት ገጽታዎች
ኢትዮጵያ ከሁለት አስር ዓመታት በላይ ስትገለገልባቸው የነበሩ የ10፣ የ50፣ እናየ100 የገንዘብ ዓይነቶችን ሙሉ ለሙሉ በመተካት አዲስ የገንዘብ ኖቶች ይፋ አድርጋለች።
በቅርቡ ይፋ የተደረጉት የብር ኖቶች ቀደም ሲል ከነበሩት በተሻለ አጠቃቀም ምቹና ረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ ተደርገው መሰራታቸው የተገለጸ ቢሆንም ተጠቃሚዎች አንዳንድ ቅሬታዎች ሲያሰሙ ተደምጧል።
በአዲሱ የ100 እና የ10 ብር ኖቶች ላይ ከላይ ወደ ታች የተዘረጋው መስመር ብሔራዊ ባንክ አስቀድሞ እንደገለፀው በአንበሳው መካከል አያልፍም።
አንዳንዱ ላይ በአንበሳው ጆሮ፣ አንዳንዶቹ ላይ ደግሞ በአንበሳው ላይ ተሰምሮ ይታያል።
ነጠብጣቡም የሚጀምረው አንዳንዱ ላይ ከብሩ ጫፍ ሌሎቹ ላይ ደግሞ ትንሽ ወረድ ብሎ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል።
ይህንን ተከትሎ እነዚህ የገንዘብ ኖቶች የተጭበረበሩ ናቸው የሚል አሉባልታ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ተጠቃሚዎች ዘንድ ሲሰራጭም እየተሰማ ነው።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የብሔራዊ ባንክ የከረንሲ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አበበ ሰንበቴ ግን አዲሶቹ የብር ኖቶች ላይ የሚታየው ልዩነት ተራ የሕትመት ችግር እንጂ ተመሳስሎ የተሠራ እንዳልሆነ ገልፀዋል።
አክለውም ይህ በገንዘቡ አጠቃቀም ላይ የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለ አስረግጠው ይናገራሉ።
ይህንን በኅብረተሰቡ ውስጥ እየተነገሩ ያሉ ሁኔታዎችን ሲያብራሩም በአዲስ የገንዘብ ኖቶች ላይ ለደኅንነት የተቀመጡ ምልክቶች ላይ የተወሰነ ልዩነት ሊኖር እንደሚችልም ምክንያቱን አስቀምጠዋል።
በተቻለ መጠን መስመሮች መኖር ካለባቸው ስፍራ ፈቀቅ ሊሉ እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ "የሕትመት ችግሩ ባይኖር ይመከራል፤ አይኖርም ግን ተብሎ አይጠበቅም" ብለዋል።
እነዚያ ምልክቶች በትክክል በአዲሱ የገንዘብ ኖት ላይ እስከተገለፀ ድረስ ያን ያህል ችግር ነው ተብሎ ሊወሰድ እንደማይችል አብራርተዋል።
ብሔራዊ ባንክ ገንዘቡ ሲታተም በቅድሚያ ያየው መኖሩን የገለፁት አቶ አበበ፣ ሕትመቱን ለሚሰሩት አካላት ያንን በተቻለ መጠን እንዲያጠቡትም ገለፃ እንደተደረገላቸው ያስታውሳሉ።
ነገር ግን ባለው ሁኔታ ማሽኑ ላይ ለህትመት ሲገባ መዛነፉ እንደተፈጠረ ይናገራሉ።
አቶ አበበ አዲሶቹን ብሮች ከቀደመው ጋር በማነጻጸርም ኀብረተሰቡ እነዚህን የደኅንነት መለያ ምልክቶች የሆኑ መስመሮች የተሰሩት ወረቀቱ ላይ በመታተም ሳይሆን ወረቀቱ ውስጥ ተሰርተው ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በባለ 50 ብር እና በባለ 100 ብር ኖቶች ላይ ያለው መስመር የታተመው በገንዘቡ ላይ መሆኑን አስታውሰው የአሁኑ ግን በወረቀቱ ውስጥ መሰራቱን ይናገራሉ።
የሚጠራጠር ተገልጋይ ካለ ብሩን በብርሃን ላይ ወስዶ በሚመለከትበት ወቅት ቀጥታ ከላይ ወደ ታች የሚወርድ መስመር እንደሚመለከት ያስረዳሉ።
አቶ አበበ እንደሚሉት ይህም ሁኔታ ብርን አስመስለው የሚሰሩ ግለሰቦች በጭራሽ ሊሰሩት በማይችሉበት ሁኔታ ዲዛይን ተደርጓል።
ሆኖም እንዲህ ዓይነት የመስመር መዛነፍ በሁሉም ኖቶች ላይ ሳይሆን ባበለ መቶ በተወሰኑ ቅጠሎች ላይ የተከሰተ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው ለአቶ አበበ ቢቢሲ ኣቀረበላቸው ጥያቄ በሁለት መቶ ብር ኖቶች ላይ የታየውን የእንግሊዝኛ ፊደላት ግድፈት ነው።
በብሩ ላይ መቶ ወይም በእንግሊዝኛው hundred ተብሎ ከተፃፉ ፊደላት መካከል ዲ(d) ኦ (0) እንደሚመስል ማስተዋል ይቻላል።
አቶ አበበ ሲመልሱም የተመረጠው ፎንት መሆኑን በማንሳት ይህ ተጠቃሚዎችን በሚያሳስት ደረጃ አለመቀመጡን አብራርተዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው ባለ መቶ ብሮች ላይ ካለው ጋር ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ነው ያሉት አቶ አበበ ፊደላቶቹ 'ፎንት' ሲመረጡ የተከሰተ መሆኑን ይናገራሉ።
እነዚህ የፊደል አጣጣሎች የተመረጠው መሆኑ ጠቅሰው የሚያመጣው ምንም አይነት ችግር እንደማይኖርም ይገልፃሉ።
ሁለት መቶ የሚለው የአማርኛ ፊደልና ቁጥሩ በአግባቡ መቀመጡን ገልፀው፣ ይህ የብር ተጠቃሚው ላይ የሚፈጥረው ችገር አለመኖሩን አረጋግጠዋል።
ማየት ለተሰናቸው የተዘጋጀው ነጠብጣብ
የአይነ ስውራን ብሔራዊ ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ወሰን አለሙ በቀድሞው ብር ላይም ሆነ በአሁኑ የብር ኖቶች ላይ የሚዳሰሱ ምልክቶች መኖራቸውን በማንሳት የአሁኑ ከቀድሞው የተሻለ መሆኑን ያነሳሉ።
ምልክቶቹ በቀኝና በግራ ጫፍ ላይ እንዳሉ የሚገልፁት አቶ ወሰን፣ ብሔራዊ ባንኩ እንዳለው ነጥቦቹ ከአስር ብር ጀምሮ እስከ ሁለት መቶ ብር ድረስ ብዛታቸው እየተለያየ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
የአይነስውር ማህበሩ ፕሬዝዳንት ለቢቢሲ እንደተናገሩት የተቀመጡት ምልክቶች በጣም የተጠጋጉ በመሆናቸው በእጅ ለመለየት አስቸጋሪ ናቸው።
ብሮቹን ለመለየት ከዚህ ቀደም ስፋቱና ቁመታቸውን ይጠቀሙ እንደነበር ገልፀው፣ የአሁኖቹ መቶ እና ሁለት መቶ ብሮች ያላቸው የመጠን ልዩነት በጣም አነስተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
አቶ አበበ በበኩላቸው ለብሔራዊ ባንኩ የመጣ እንዲህ አይነት አስተያየት እስካሁን ድረስ አለመኖሩን ገልፀው ፤ የተቀመጡት ምልክቶች ሌሎች አገራትም የሚጠቀሙባቸው መሆናቸውን አስረድተዋል።
ቴክኖሎጂው በትክክል ማየት የተሳናቸው ሰዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ ተብሎ መቀመጡን በመግለጽ በባለመቶው ላይ ስድስት፣ በባለ ሁለት መቶው ላይ ደግሞ ስምንት ምልከቶች መኖራቸውን ገልፀዋል።
አቶ ወሰን እነዚህ ምልክቶች ብሩ የወረቀት በመሆኑ ሊፈገፈጉ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
አቶ አበበ ግን የገንዘቡ ጥራትም ቢሆን ሌሎች አገራት የሚጠቀሙባቸው ጥራቱን የጠበቀ ወረቀት መሆኑን ያስረዳሉ።
በርግጥ በሌሎች አገራት ላይ የፕላስቲክ ገንዘቦች ያሉ ቢሆኑም ኢትዮጵያ ግን በአሁኑ ሰዓት እነዚያን ለመጠቀም የማትችልባቸው የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን አንስተዋል።
የገንዘብ ሕትመት ሚስጥራዊነቱን በጠበቀ መልኩ እንደሚካሄድ ተናግረው የሚኖሩ ጉድለቶች በሚመጡ አስተያየቶች በሂደት እንደሚስተካከሉ ገልፀዋል።
ሕትመት የአንድ ጊዜ ክንውን አይደለም በማለትም ባንኩ የሚቀርቡ አስተያየቶችን ካመነባቸው በሂደት ማስተካከያ እንደሚደርግ ተናግረዋል።
ገንዘቡ ላይ የሚታዩ የደኅንነት መጠበቂያ ምልክቶች ምንድን ናቸው?
አዳዲሶቹ የገንዘብ ኖቶች አስመስለው የሚሰሩ ሐሰተኛ የብር ኖቶችን ለመከላከልና ለመለየት በሚያስችል ሁኔታ የተለያዩ የደኅንነት መጠበቂያ ገጽታዎች እንዲኖሯቸው ተደርጓል።
ለአይነ ስውራንም የእውቅና ምልክት ያላቸው ሲሆን የብሩን ዋጋ በእጅ ዳሰሳ ማወቅ የሚችሉበት የደኅንነት መጠበቂያ ያለው ነው።
በተመሳሳይ ገንዘቡ ወደ ላይ ወይንም ወደታች ሲዞር የሚንቀሳቀስ ደማቅ የቀለም ፍንጣቂ የደኅንነት መጠበቂያ ምልክት እንዳለውም ተነግሯል።
እንደ ብሔራዊ ባንክ ገለፃ ከሆነ አዳዲሶቹ ገንዘቦች የሚሽከረከር ደማቅ ቀለም ኮኮብ አዲስ የደህንነት መጠበቂያ ክር፤ በክሩ ውስጥም NBET፣ ኢብባ እና ገንዘቡ አይኖቶች ተፅፈው ይገኙበታል ነው የተባለው።
ገንዘቡ ወደ ብርሃን አቅጣጫ ተደርጎ ሲታይ በላይ ላይ ከሚገኘው ምስል ፊት ለፊት ተመሳሳይ ደብዛዛ ውሃ መልክ ያለው ምልክት እንደሚታይ ተጠቁሟል።
የብር ኖቶቹ በብርሃን አቅጣጫ ሲታይ ኳስ መሳይ ምልክት ከኖቶቹ በስተኋላ ካለው ተመሳሳይ ምልክት ጋር በፍፁም ትይዩ ሆነው በአንድ ቦታ ላይ ያርፋሉ።
እንዲሁም አንበሳው ምስል ራስ ላይ 'አልትራቫዮሌት ጨረር' ሲበራበት ወደ ቢጫነት የሚለወጥ' ፍሎረሰንት' ምልክት አለው ተብሏል።
ኖቶቹን በመቀየሩ ሥራ ለህትመት ብቻ በአጠቃላይ 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገ ተነግሯል።
ከቀለም አንጻር አዲሱ ባለ 200 ብር ኖት ሐምራዊ፣ ባለ100 ብር ኖት ውሃ ሰማያዊ፣ ባለ50 ብር ኖት ቀይ ብርቱካናማ፣ ባለ10 ብር ኖት ደግሞ አረንጓዴ ቀለም አላቸው።