ቤንሻንጉል ጉሙዝ፡ መንግሥት የዜጎችን ደህንነት እና ሰላም እንዲጠብቅ ኢሰመጉ ጥሪ አቀረበ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሰሞኑ በደረሰው ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውን፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና አስገድዶ መሰወር (እገታ) እንደተፈፀመባቸው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፣ ኢሰመጉ በትናንትናው ዕለት፣ መስከረም 9፣ 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በክልሉ፣ ነሃሴ 29 እና 30 እንዲሁም ጳጉሜ 1 እና 2 ቀን ባሉ ቀናት ጥቃቶቹ እንደተፈፀሙ ያስታወሰው መግለጫው በመተከል ዞር ስር አስተዳደር ባሉት ጉባ፣ ዲባጢ፣ ቡለን እና ወንበራ ወረዳዎች በርካታ ነዋሪዎች ኢላማ እንደተደረጉም በስፍራው ከሚገኙ እማኞች ሰበሰብኩት ያለውን መረጃ ዋቢ አድርጓል።
በነዚህ አካባቢዎች ንፁኃን ሰዎች በቀስት፣ በስለት እና በጦር መሳሪያ በታገዙ እጅግ አሰቃቂ ብሎ የጠራው ሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተፈፅሟል ብሏል።
በነዚህ በርካታ ቀበሌዎች ላይ ጥቃቱን ያደረሱት ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች እንደሆኑ አስፍሮ በርካቶችም ባለው ስጋት ምክንያት ከመኖሪያ ስፍራቸው እንደሸሹ ኢሰመጉ አስታውቋል።
ጥቃቱ የደረሰባቸው አካባቢዎች ከዚህ ቀደምም ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የደረሱበት እንደሆነ ያስረዳው የኢሰመጉ መግለጫ በፌደራል መንግሥትም ሆነ በክልሉ መንግሥት በዘላቂነት ችግሩን ለመቅረፍ ስራዎች እንዳልተሰሩ ጠቁሟል።
የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግሥት አልፎ አልፎ ከሚወስዷቸው የህግ ማስከበር ስራዎች በዘለለ ችግሩን ከስር መሰረቱ ባጤነ መልኩ ወደ ዘለቄታዊ መፍትሄ አልሄዱም ብሏቸዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በደረሱ ጥቃቶች ላይ ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ በተለያየ ደረጃ ላይ ባሉ አስተዳደሮች ላይ ተገቢው እርምጃ ባለመወሰዱ ምክንያት እንዲህ አይነት ጥሰቶች እንደገና ለመድረሳቸው ምክንያት መሆኑን ኢሰመጉ እንደሚያምን አስፍሯል።
"በየደረጃው ያሉ የፀጥታ ኃይሎች እና የመንግሥት የፍትህ ተቋማት ችግሩ እንዳይከሰት አስቀድሞ የመከላከል ከተከሰተም በኋላ በአፋጣኝ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ የማስተካከል ህገ መንግሥታዊ ኃላፊነታቸውን በሚገባ ባለመወጣታቸው ንፁኃን ሰዎች የተደጋጋሚ ጥቃቶች ሰለባ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ለመረዳት ችለናል" ብሏል።
ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ኢሰመጉ የመፍትሄ ኃሳብ ያላቸውን አቅርቧል። ጥቃቱን የፈፀሙት ለፍትህ እንዲቀርቡ፣ ተጎጂ ግለሰቦች ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደረግላቸው እና ተገቢው የሞራል እና የገንዘብ ካሳ እንዲሰጣቸው ኢሰመጉ ጠይቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የክልሉና የፌደራል መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች የጀመሩትን ህግ የማስከበር እንቅስቃሴ አጠናክረው በመቀጠል ጠንካራ ህጋዊ እርምጃዎችን በመውሰድ እንደሚገባም አስፍሯል።
"የዜጎችን በህይወት የመኖር የአካል ደህነነት ነፃነት እንዲሁም ሰላም እና ደህንነቱ በተጠበቀ በማንኛውም አካባቢ የመኖር ህገ መንግሥታዊ መብቶቻቸውን በምልዓት እንዲያረጋግጡ" ኢሰመጉ አሳስቧል።
የክልሉም ሆነ የፌደራል መንግሥት እነዚህን ተደጋጋሚ ጥቃቶች አስቀድሞ መከላከል የሚያስችል መዋቅር መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ያሳሰበው መግለጫው ለተደጋጋሚ ሰብዓዊ ጥሰቶቹ ዘላቂ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል ብሏል።
ከሰሞኑም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ ላይ በመግለጫው ላይ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጳጉሜ 1/2012 ዓ.ም እንዲሁም ከመስከረም 4 አስከ መስከረም 10/2013 ዓ.ም መካከል ባሉት ቀናት ውስጥ ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከክልሉ መንግሥት ለማረጋጥ መቻሉን አመልክቷል።
ይህንንም ተከትሎ ቢያንስ በሁለት ዙር በተፈጸሙ ጥቃቶች ባልታጠቁ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ግድያዎች መፈፀማቸውን እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መፈናቀላቸውን በስፍራው ከሚገኝ አንድ መንግሥታዊ ምንጭ መረዳት እንደቻለ ኮሚሽኑ መግለፁ የሚታወስ ነው።
በክልሉ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖር በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስ እና በክልል የጸጥታ ኃይሎች ሰላምን ለማስጠበቅ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንደሚያበረታታም አስታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ በደቡብ ክልል በኮንሶ ዞን ካራትና ኮልሜ ወረዳዎች እና በአሌ ልዩ ወረዳ መካከል ባሉ አዋሳኝ ቀበሌዎች በተከሰተው ግጭት በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፣የአካል ጉዳት ደርሷል እንዲሁም ቤት ንብረታቸው ወድሟል።
በዋነኝነት ለዓመታት ሲንከባለል የመጣው የወሰን አካለል ጋር በተያያዘ በሚነሱ ግጭቶች የሰዎች ህይወትን መጥፋት እያስከተለ ነው፤ ከባለፈው ዓመት ኃምሌ ጀምሮም ግጭቱ እንዳልበረደ አስታውሷል።
እነዚህን ግጭቶች በተመለከተ ኢሰመጉም መንግሥት መሰረታዊና ዘለቄታዊ መፍትሄ እንዲያበጅም ለመንግሥት ጥሪ አቅርቧል።












