ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ተመራማሪው በብራዚል ጫካ በሚወዳቸው ነባር ጎሣዎች ተገደለ
ሬይሊ ፍራንሲስካቶ ይባላል። 56 ዓመቱ ነው። ከትናንተ በስቲያ ረቡዕ በብራዚል፣ ሰሜን ምዕራብ አማዞን፣ ልዩ ስሙ ሮንዶኒያ ግዛት ነው የተገደለው።
አሟሟቱም በነባር የጫካ ነዋሪ ጎሣዎች በተተኮሰበት ቀስት ደረቱ ላይ ተመትቶ ነው።
ግለሰቡ እውቅ የአማዞን ነባር የአገሬው ጎሣዎች (indigenous tribes) ተመራማሪ ሲሆን በዚያ ዕለትም ወደ ነባር የአገሬው ጎሣዎቹ እየሄደ የነበረው ለምርምር ሥራ ነበር።
ፍራንሲስኮ የመንግሥት አገር በቀል ጉዳዮች ኤጀንሲ ውስጥ ነበር የሚሰራው።
የዐይን እማኞች እንደሚሉት ሚስተር ፍራንሲስካቶ ወደነዚህ ነባር ጎሣዎቹ በሚጠጋበት ጊዜ በፖሊስ ታጅቦ ነበር።
ነገር ግን ዛፍ ላይ ተንጠልጥለው ይጠብቁ ከነበሩ ከነዚህ ነባር የጫካው ነዋሪ ጎሣዎች ድንገት የተተኮሰበት ቀስት ደረቱ ላይ ተሰክታ ለህልፈት አብቅተዋለች።
በስፍራው የነበሩ እማኞች እንዳሉት ከሆነ ፍራንሲስካቶ በቀስት ከተመታ በኋላም ቢሆን ቀስቱን ከደረቱ ነቅሎ ለመሸሽ መጠነኛ ጥረት አድርጓል። ደረቱ ላይ የተሰካውን ቀስት ነቅሎ ወደ 50 ሜትር እንደሮጠ ግን አልቻለም፤ ተዝለፍልፎ ወደቀ።
በአካባቢው በፎቶግራፍ ጋዜጠኝነት የሚሰራው ጋብሬል ኡቺዳ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደተናገረው ሚስተር ፍራንሲስ ወደ አካባቢው የሄደው ካውታሪዮ የሚባለውንና ከዓለም ተገሎ የሚኖረውን ጎሣ ለመጎብኘት ነበር።
ፎቶ አንሺው ኦቺዳ እንደሚለው ይህ ጎሣ በአመዛኙ ሰላማዊ እንደሆነ ነው የሚታወቀው፤ በዚያ ዕለት ግን የጎሣው ተዋጊ ቡድን (መቺ ኃይል) ምናልባት አደን ወጥቶ ነበር፤ 5 ወንዶችን የያዘው የጎሣው ተዋጊ ቡድን ነው ፍራንሲስካቶን የገደለው ብሏል።
ነባር የአማዞን ነዋሪዎች ከተቀረው ዓለም ለሚመጡ እንግዶች መልካም አቀባበል በማድረግ እምብዛምም አይታወቁም። ወራሪና ተናኳሽ አድርገው ነው ቀሪውን ዓለም የሚስሉት። ስለዚህ አደጋ የመጣል ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
ካኒንዴ ኢትኖ ኢንቫይሮመንታል ዴፌንስ አሶሲየሽን የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅትን እንዲመሰረት ያደረገው ሟቹ ፍራንሲስካቶ ነበር።
ይህ ድርጅት ነባር የአገሬው አማዞን ነዋሪዎችን በመጠበቅና በመንከባከብ ሲሰራና ሲያግዝ ኖሯል።
ድርጅቱ በፍራንስካቶን ሞት ከፍተኛ ሐዘን ተሰምቶታል። ይኸው ግብረ ሰናይ ድርጅት የፍራንስካቶን ሞት ተከትሎ ለዜና አውታሮች እንደተናገረው ነባር የጫካ ነዋሪዎች ብዙውን ጊዜ ማን ወዳጃቸው ማን ጠላታቸው እንደሆነ ስለማይለዩ ነው ወዳጃቸው ፍራንስካቶ ላይ አደጋ የጣሉት።
በአመዛኙ ነባር የአገሬው ጎሣዎች በጫካ ራሳቸውን አግልለው ስለሚኖሩ ለባዳዎች የጠላትነት መንፈስ ይዘው ነው የሚቆዩት።
ነባር የአገሬው ጎሣዎቹ በተለይ ከ2019 ወዲህ ማለትም ቦልሶናሮ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የአያት የቅድመ አያቶቻቸው መሬት እየተቀማ ለልማት እየዋለባቸው ስለሆነ ባልተለመደ መልኩ ቁጡ ሆነዋል።
ሕገ-ወጥ ማዕድን አውጪዎች፣ እና ዛፍ ቆራጮች አካባቢያቸውን እየወረሩ ስለሆነ ለተቀረው ዓለም ጥላቻን እያጎለበቱ ሳይመጡ አልቀረም።
ምንም እንኳ ፍራንሲስካቶ ይሰራበት የነበረው ፉናይ የተባለው የመንግሥት ኤጀንሲ እነዚህን ነባር ነዋሪዎች ለመጠበቅ የተቋቋመ ቢሆንም ቦልሶናሮ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ግን ኤጀንሲው በቂ በጀት እንኳ አይመደብለትም ነበር።
ይህም በመሆኑ ሕገ-ወጥ የደን ጨፍጫፊዎች፣ ማዕድን አውጪዎችና መሬት ወራሪዎች በአማዞን ጫካ ጉዳት ሲያደርሱ ዝም ይባላሉ።
ቦልሶናሮ ወደ ሥልጣን ሲመጡ አንድ አገር የሚሸፍነውን አማዞን ጫካን በከፊል አውድሞ ለልማት ለማዋል ለደጋፊዎቻቸው ቃል ገብተው ነበር።
‹‹አማዞን ተጠብቆ ብቻ መቆየት የለበትም፤ እየመነጠርን ለልማት እናውለዋለን›› ሲሉ ይዝታሉ፣ ቦልሶናሮ በተደጋጋሚ።
አማዞን ጫካ የምድራችን ሳምባ እየተባለ ነው የሚጠራው። ያም ሆኖ በየዓመቱ በተደጋጋሚ የእሳት አደጋ ይደርስበታል።
በአማዞን ጫካ ውስጥ ከመቶ በላይ የሚሆኑ ከውጭው ዓለም እምብዛምም እውቂያ የሌላቸው ነባር የአገሬው ጎሣዎች ይኖራሉ።
ሟቹ ፍራንሲስካቶ እጅግ በሚወዳቸው ነባር ጎሣዎች ሕይወቱ ብታልፍም እነሱን ከወራሪዎች ለመጠበቅ 30 ዓመታትን ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል አገልግሏል።