ከሃጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ ሁለት ሰዎች መያዛቸውን ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ

የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎች በተከሰተ አለመረጋጋትና ግጭት ቢያንስ የ50 ሰዎች ህይወት መጥፋቱን የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣን አስታወቁ።
የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽ ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ ለቢቢሲ ከሃጫሉ ሞት ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ተቀስቅሶ በነበረው ተቃውሞ ከሃምሳ በላይ ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች መቁሰላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
አክለውም የሞቱት በተቃውሞ የተሳተፉ እንዲሁም በጸጥታ ማስከበር ሥራ ላይ የነበሩ ኃይሎች መሆናቸውን ለሮይተርስ ገልጸዋል።
በሰው ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች የንግድ ተቋማትና መሥሪያ ቤቶች በእሳት የመቃጠል ውድመት እንደደረሰባቸው አቶ ጌታቸው አረጋግጠዋል።
አቶ ጌታቸው በሰውና በንብረት ላይ ስላጋጠመው ጉዳት ለሮይተርስ "ለዚህ አልተዘጋጀንም ነበር" ሲሉ ተናግረዋል።
በተያያዘ ዜናም ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ሁለት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታወቀ።
ትናንት ማታ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና የኦሮሚያ ፖሊስ በጋራ በሰጡት መግለጫ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባል የሆነው ጃዋር መሐመድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን ገልፀዋል።
አቶ ጃዋር እና ሌሎች 35 ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ከድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የአስከሬን ሽኝት መስተጓጎልና ከአንድ የፖሊስ አባል ግድያ ጋር በተያያዘ መሆኑ ተገልጿል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን እና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ የጃዋር ጠባቂዎች ይዘውት የነበሩት የጦር መሳሪያዎች እና መገናኛ ሬዲዮችም መያዛቸውን አመልክተዋል።
በዚህም መሰረት 8 ክላሽ፣ 5 ሽጉጥ እና 9 የሬዲዮ መገናኛዎች ከጃዋር ጠባቂዎች ላይ ፖሊስ መያዙን ተገልጿል።












