በዩናይትድ ኪንግደም ኮሮናቫይረስ በተያዙ ህፃናት ላይ ያልተለመደ ምልክት መታየቱ ተገለፀ

የብሔራዊ ጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) የሕክምና ባለሙያዎች ሕፃናት ላይ ያልተለመደ ነገር ግን አደገኛ የሆነ ምልክትን በሚገባ እንዲመለከቱ አስጠነቀቀ። ይህ ለዶክተሮቹ የተገለፀው ምናልባት ያልተለመደው ምልክት የኮሮናቫይረስ ኢንፌክሽን ምልክት ሊሆን ይችላል በሚል ነው።

ለጠቅላላ ሐኪሞች በአስቸኳይ የተላከው መልዕክት እንደሚለው ከሆነ በሎንዶንም ሆነ በዩናይትድ ኪንግደም የተለያዩ አካባቢዎች በጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገኙ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሕፃናት ያልተለመዱ ምልከቶች እንደሚታይባቸው ይጠቅሳል።

ይህም ከፍሉ ምልክት በተጨማሪ "የተለያዩ አካል ክፍሎች በአንድ ላይ መቆጣት"መሆኑን በመጥቀስ እንዲህ አይነት ምልክት ከታየባቸው ህፃናት መካከል አንዳንዶቹ በኮሮናቫይረስ ተይዘው መገኘታቸውን ይገልፃል።

በርግጥ ቁጥራቸው ዝቅተኛ ነው ከማለት ውጪ ምን ያህል ህፃናት እንዲህ አይነት ምልክት እንዳሳዩ የተገለፀ ነገር የለም።

በእንግሊዝ የብሔራዊ ጤና አገልግሎት (ኤንኤችኤስ) ሐኪም የሆኑት ስቴፈን ፖዊስ እንዲህ ያልተለመደ እና ጽኑ ሕመም በህፃናት ላይ ስለመታየቱ የተለያዩ ሪፖርቶችን ማየታቸውን ይናገራሉ።

" እነዚህን ሪፖርቶች የተመለከትነው ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ነው። ባለሙያዎቻችንን ጉዳዩን አጽንኦት ሰጥተው በአስቸኳይ እንዲመለከቱት ጠይቀናል" ብለዋል።

በእንግሊዝ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት በኩል የወጣው ሪፖርት በሕፃናት ላይ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የተለያዩ አካላት መቆጣት " እየጨመረ የመጣ አሳሳቢ ጉዳይ" ብሎታል።

እነዚህ በተለያየ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህጻናት በከፍተኛ ሁኔታ መታመማቸው ተገልጿል። ከፍተኛ የሆነ ሙቀት፣ ዝቅተኛ የደም ግፊት፣ የሰውነት ሽፍታ እንዲሁም ለመተንፈስ መቸገር እንደሚታይባቸው ተገልጿል።

አንዳንዶቹም የሆድ እቃ ህመም፣ ማስመለስ ወይንም ተቅማጥ፣ የልብ አካባቢ ማቃጠል እንዲሁም ያልተለመደ የደም ውጤት እንደሚስተዋልባቸው ተገልጿል።

ባለሙያዎች እነዚህ ምልክቶች የሚታዩት ሰውነት የተለያዩ ኢንፌክሽኖችን በሚዋጋበት ወቅት መሆኑን ይገልፃሉ።

የተላለፈው መልዕክት እንዲህ አይነት ምልክት የሚያሳዩ ህፃናት በፍጥነት ሕክምና ማግኘት አለባቸው ይላል።

ባለሙያዎች አክለውም በጣም ጥቂት ቁጥር ያላቸው ህፃናት ብቻ በኮሮናቫይረስ በጽኑ ታመው ታይተዋል፤ ከመላው ዓለም የሚመጣ መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ላይ በቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ቁጥር አንፃር ህፃናት በጣም ጥቂት ናቸው።

ዶ/ር ናዚማ ፓታን በካምብሪጅ የህጻናት ጽኑ ሕሙማን አማካሪ ሲሆኑ በስፔንና በጣሊያን ያሉ ባለሙያዎች ተመሳሳይ ምልክት ያሳዩ ሕፃናትን ማግኘታቸውን ሪፖርት ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

" በአጠቃላይ ህፃናት ኮሮናቫይረስን ተከትሎ የሚመጣን ከባድ የሳንባ ኢንፌክሽን የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛ መሆኑን አስተውለናል፤ ወደ ጽኑ ሕሙማን ክፍልም የገቡ ህፃናት ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው" ብለዋል።

አሁን የምንጠብቀው ይላሉ ዶ/ር ናዚም እንዲህ አይነት ምልክት የሚያሳዩ ህፃናት ከባክቴሪያ ኢንፌክሽን ጋር የተያያዘ እና ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥለው (toxic shock syndrome) እና የደም ቧንቧንና ልብን የሚያጠቃው የካዋስኪ በሽታ ምልክቶችን ማሳየት አለማሳየታቸውን ነው ብለዋል።