ፌስቡክ ጥንዶች ብቻ በሚስጥር የሚያወሩበት መተግበሪያ ይፋ አደረገ

ፌስቡክ ጥንዶች ለብቻቸው የሆድ የሆዳቸውን የሚያወሩበት መተግበሪያ ይፋ አደረገ።

ይህ አዲሱ መተግበሪያ ቲዩንድ (Tuned ) የሚሰኝ ሲሆን ጥንዶች በጋራ መልዕክት እንዲለዋወጡ፣ ሙዚቃ እንዲጋሩ እናም ዲጂታል የሆነ የፎቶ አልበም እንዲያዘጋጁ የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።

ቲዩንድ በፌስቡክ አዳዲስ ምርቶች መሞከሪያ ቡድን አባላት የተሰራ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ትኩረቱን ያደረገውም አዲስ ማህበራዊ ሚዲያን ሀ ብሎ መፍጠር ነው።

መተግበሪያው ለጥንዶች "የብቻ ዓለም" ይሆናል የተባለ ሲሆን እንደዋትስ አፕ ግን መልዕክታቸው በሶስተኛ ወገን እንዳይጠለፍ ማድረግ የሚያስችል ቴክኖሎጂ እንዳልተሰራለት ተገልጿል።

ከዚህ ይልቅ ቲዩንድ የፌስቡክ ተመሳሳይ የሆነ የዳታ ፖሊሲ ይከተላል፤ ይህም የደንበኞቹን አጠቃቀምና ባህሪ መረጃ በመሰብሰብ ተጠቃሚውን ታላሚ ያደረገ ማስታወቂያ መልቀቅ ላይ ትኩረት ያደርጋል።

ይህም የዳታ ፖሊሲ ተጠቃሚዎች የግል መረጃቸውን ወይም ምስላቸውን በመተግበሪያው እንዳያጋሩ ሊያደርጋቸው ይችላል ተብሏል።

ፌስ ቡክ አዲስ ስላስተዋወቀው ስለዚህ ምርት ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ አልሰጠም።

ይህ መተግበሪያ በአሜሪካና በካናዳ ላሉ የአይፎን ስልክ ተጠቃሚዎች ብቻ የተለቀቀ ሲሆን የፌስቡክ አካውንት እንዲኖር አይጠይቅም ተብሏል።

ፌስቡክ በ2018 ወደ ጥንዶች ዓለም እንደሚገባ አስታውቆ ነበር። እስካሁን ድረስ የፍቅር ጓደኛ አፈላላጊ የሆኑት ቲንደርንና በምብልን ለመፎካከር በ20 አገሮችም የሚሰራ መተግበሪያ አለው።

ይህ አዲሱ መተግበሪያ ግን ከዚህ የተለየ ነው ተብሏል።

ይህ አዲሱ የፌስቡክ ምርት ከሌላ መልዕክት መለዋወጫ አገልግሎቶች አይለይም።

ተጠቃሚዎች ስልካቸውን በመጠቀም የሚፈልጉትን ሰው መገናኘት የሚችሉ ሲሆን ወዳጅነት ከመሰረቱም በኋላ ምስልና ድምጽ በቀላሉ መላላክ ይቻላል።