ኮሮናቫይረስ: ሐሰተኛ መረጃ እንዳይስፋፋ ምን ልናደርግ እንችላለን?

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ሐሰተኛ መረጃዎች በይነ መረብን እያጥለቀለቁት ይገኛሉ። ባለሙያዎች ደግሞ ኅብረተሰቡ "መረጃ ማጥራትን" እንዲለማመድ ጥሪ አቅርበዋል። አሳሳች መረጃ እንዳይስፋፋ ምን ማድረግ ይችላሉ?

1. ቆም ብለው ያስቡ

ቤተሰቦችዎን እና ጓደኞችዎን መርዳት ይፈልጋሉ። አዲስ ምክር ባገኙ ቁጥር በኢሜይል፣ በዋትስአፕ ፣ በፌስቡክ ወይም በትዊተር በፍጥነት ሊያካፍሏቸው ይችላሉ።

እንደባለሙያዎች ከሆነ የተሳሳተ መረጃን ለማቆም ማድረግ የሚችሉት አንድ ቀላል ነገር ቆም ብሎ ማሰብ ነው።

ስለመረጃው ጥርጣሬ ካለዎት ለአፍታ ቆም ብለው በደንብ ይመልከቱት።

2. ምንጭዎን ያረጋግጡ

መረጃውን ከማስተላለፍዎት በፊት መረጃው ከየት እንደመጣ ይጠይቁ።

ምንጩ "የጓደኛ ጓደኛ" ወይም "የአክስቴ ባልደረባ ጎረቤት" ከሆነ መረጃው ትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ ይገባል ማለት ነው።

በቅርቡ ከአንድ "ሁለተኛ ዲግሪ ካለው አጎቴ" የሚል አንድ አሳሳች መረጃ በፍጥነት የተዛመተበትን መንገድ ለመመልከት ችለናል።

በመረጃው ላይ ያሉት የተወሰኑት ጉዳዮች ትክክለኛ ነበሩ። ለምሳሌ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት እጅ መታጠብን ያበረታታል።ሌሎቹ ነገሮች ግን ጎጂ ከመሆናቸውም በተጨማሪ ያልተረጋገጡና በሽታውን ለመመርመር የሚረዱ ናቸው የተባሉ ዝርዝሮች ቀርበውበታል።

"አስተማማኝ የመረጃ ምንጮች እንደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የዓለም ጤና ድርጅት ወይም የአሜሪካው የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ያሉ የሕዝብ ጤና ተቋማት ናቸው" ሲሉ መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገውና የመረጃዎችን ትክክለኛነት የሚያረጋግጠው 'ፉል ፋክት' የተባለው ድርጅት ምክትል አርታኢ ክሌይር ሚልን ያስረዳሉ።

3. ሐሰተኛ ሊሆን ይችላል?

አቀራረቡ አሳሳች ሊሆን ይችላል።

የቢቢሲ አማርኛ እና የመንግሥትን ጨምሮ ኦፊሴላዊ አካውንቶችን፣ ድረ ገጾች እና ባለሥልጣኖችን ገጽ ማስመሰል ይቻላል። ፎቶ በማንሳት መረጃው ከታመነ አካል የመጣ እንዲመስልም ሊደረግ ይችላል።

የታወቁ እና የተረጋገጡ አካውንቶችና ድረ ገጾችን ይጎብኙ። መረጃውን በቀላሉ ማግኘት ካልቻሉ ምናልባት ሐሰተኛ ሊሆን ይችላል። ጽሑፉ፣ ቪዲዮው ወይም ገጹ አጠራጣሪ ምናልባትም ሐሰተኛ ይሆናል።

ካፒታል ሌተርስ (Capital letters) እና ወጥያልሆኑ የፊደላት ቀርጾች (fonts) አጠቃቀም መረጃዎችን ትክክለኛነት በሚያረጋግጡ ባለሙያዎች መረጃው አሳሳች ሊሆን እንደሚችል እንደአመላካች ከሚጠቀሙባቸው ነጥቦች አንዱ መሆኑን የፉል ፋክት ምክትል አርታኢ ክሌይር ሚልን ይገልጻሉ።

4. አውነት ስለመሆኑ እርግጠኛ አይደሉም? መረጃውን አያጋሩ

እውነት "ሊሆን ይችላል" በሚል ብቻ መረጃዎችን አያስተላልፉ። በዚህ ምክንያት መልካም ከማድረግ ይልቅ ጉዳት እያደረሱ ይሆናል።

ብዙ ጊዜ መረጃዎችን የምንለጥፈው እንደሐኪሞች ወይም የህክምና ባለሙያዎች ያሉ ባለሙያዎች ባሉባቸው ቦታ ነው። ይህ ጥሩ ሊሆን ይችላል።

ነገር ግን ስለጥርጣሬዎ ግልፅ መሆንዎን ያረጋግጡ። ያጋሩት ፎቶ ወይም ጽሑፍ ከአውዱ ውጭ ሊወሰድ ስለሚችልም ይጠንቀቁ።

5. እያንዳንዱን እውነታ በተናጥል ይፈትሹ

ዋትስአፕ ላይ እየተሰራጨ ያለ የድምፅ ማስታወሻ አለ። በማስታወሻው ውስጥ የምትናገረው ግለሰብ ሆስፒታል ውስጥ የሚሠራ "ጓደኛ ካለው ባልደረባ" ያገኘቻቸውን ምክሮች እየተረጎመች ስለመሆኑ ትናገራለች። ይህም በደርዘን በሚቆጠሩ ሰዎች አማካይነት ከዓለም ዙሪያ ወደ ቢቢሲ ተልኳል።

ሆኖም ትክክለኛ እና ትክክል ያልሆኑ ምክሮች የተደባለቀቡት ነበር።

በጣም ጠቃሚ የሆኑ ምክሮችን ዝርዝር በሚያገኙበት ወቅት በመሃል በሚያገኙት አንድ ትክክለኛ ምክር (ለምሳሌ እጅ መታጠብ ጠቃሚ ስለመሆኑ በመገለጹ) ብቻ ሁሉንም ትክክል ነው ብሎ ማመን ቀላል ነው።

ግን ሁሌም እንደዚያ አይደለም፤ ይጠንቀቁ!

6. ከስሜታዊ መረጃዎች ይጠንቀቁ

እንደእውነቱ ከሆነ ፍርሃት፣ ቁጣ፣ ጭንቀት ወይም ደስታ የሚፈጥሩብን ስሜታዊ ነገሮች ናቸው በብዛት የሚሰራጩት።

"ፍርሃት ሐሰተኛ መረጃዎች በበፍጥነት እንዲዛመቱ ከሚያደርጉ ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ ነው" ሲሉ ጋዜጠኞች በበይነ መረብ ሐሰተኛ መረጃዎችን እንዲከላከሉ የሚያግዘው 'ፈርስት ድራፍት' የተባለው ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ክሌይር ዋርድል ይገልጻሉ።

ድርጊትን የሚያበረታቱ አስቸኳይ ጥሪዎች ጭንቀትን ለማነቃቃት የተቀየሱ በመሆናቸው ይጠንቀቁ።

"ሰዎች የሚወዷቸው ሰዎች ደኅንነት የተጠበቀ እንዲሆን ለመርዳት ይፈልጋሉ" ስለዚህ 'ቫይረሱን ለመከላከል የሚረዱ ምክሮች' ወይም 'ይህን የጤና ተጨማሪ ምግብ ይውሰዱ' የሚሉ መረጃዎችን ሲመለከቱ፤ "የሚወዷቸውን ሰዎች ለመርዳት የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ይፈልጋሉ "ትላለች ክሌር።

7. ስለአንድ ጉዳይ ያለንን ወገንተኝነት አንዘንጋ

የሆነ ነገር የሚያጋሩት እውነት እንደሆነ ስላወቁ ነው ወይስ በጉዳዩ ስለተስማሙ?

በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ዙሪያ ጥናት የሚሰራ ማዕከል የምርምር ዳይሬክተር የሆኑት ካርል ሚለር እንደሚሉት በአብዛኛውን ጊዜ የምናጋራቸው መረጃዎች ያለንን እምነታችንን የሚያጠናክሩትን ነው።

"በንዴት ጭንቅላታችንን በምንወዘውዝበት ወቅት ነው በጣም ተጋላጭ የምንሆነው። በዚህ ወቅት ነው ከምንም ነገር በላይ በይነመረብ ላይ የምንሠራውን በሙሉ ማዘግየት ያለብን" ብለዋል።