ቢልጌትስ ከማይክሮሶፍት የቦርድ አመራርነቱ ወረደ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ማይክሮሶፍትን ከመሰረቱት አንዱ የሆነው ቢልጌትስ ከኩባንያው የቦርድ አባልነቱ በበጎ አድራጎት ስራዎቹ ላይ ሰፊ ጊዜ ለማሳለፍ በሚል መልቀቁ ተነገረ።
ቢልጌትስ በጤና፣ የልማት ስራዎች፣ ትምህርትና የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት የሚሰሩ ስራዎች ላይ ማተኮር እንደሚፈልግ ተናግሯል።
ጌትስ ከማይክሮሶፍት የዕለት ተዕለት ስራውን የለቀቀው እአአ በ2008 ነበር።
ጌትስ ይህንን ውሳኔውን ሲያሳውቅ ኩባንያው" ሁሌም የሕይወቴ ወሳኝ አካል ሆኖ ይቀጥላል" በማለት በአመራሩ ላይ ያለውን ተሳትፎ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ነገር ግን በማለት" ቀጣዮን መስክ ደግሞ ወዳጅነትንና አጋርነትን ለመፍጠር፤ እጅግ ለምኮራባቸው ሁለት ኩባንያዎች የማበረክተውን ለመቀጠል፣ እንዲሁም የዓለም ትልልቅ ተግዳሮቶች የሆኑትን በአግባቡ ቅደም ተከተል አስይዤ ለመስራት እንደ ወሳኝ ነጥብ አየዋለሁ" ብሏል።
ቢል ጌትስ በፎርብስ ከአማዞን መስራች ጄፍ ቤዞስ ቀጥሎ ሀብታም ሲሆን፣ አጠቃላይ ሀብቱ 103.6 ቢሊየን ዶላር ተተምኖ የዓለማችን ሁለተኛው ከበርቴ ሆኗል ።
ሀብቱን ያካበተው ለግል መጠቀሚያነት የሚያገለግሉ የኮምፒውተር ሶፍትዌሮችን በማምረት ነው።
ቢል ጌትስ ማይክሮሶፍትን ከልጅነት ጓደኛው ፖል አለን ጋር በመሆን የመሰረተ ሲሆን በወቅቱ የየኒቨርስቲ ትምህርቱን በሟቋረጥ ነበር ወደዚህ ስራ የተሰማራው።















