"በኮሮናቫይረስ ተያዙ ስለተባሉት ኢትዮጵያዊያን ለጊዜው የምናውቀው ነገር የለም" በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከትናንት በስቲያ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስት በኮሮናቫይረስ ተያዙ ከተባሉ የተለያዩ አገር ዜጎች መሀል ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን የዚያው አገር የጤና ሚኒስቴር መግለጹ ይታወሳል።
ይህንኑ በተመለከተ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጡ ከቢቢሲ የተደወለላቸው በአቡዳቢ የአምባሳደሩ ተወካይ ወ/ሮ ኑሪያ መሐመድ "እኛም እንደናንተው በሚዲያ ከመስማት ውጭ ምንም መረጃው የለንም" ያሉ ሲሆን ዛሬ (እሑድ) ግን ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ እንዲሰጣቸው ኦፊሳሊያዊ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
ለምንድነው ጥያቄውን ለማቅረብ የዘገያችሁት ተብለው የተጠየቁት በአቡዳቢ የኢትዮጵያ ተጠባባቂ ሚሲዮን መሪ (charge' d' affaires) የአምባሳደሩ ተወካይ ኑሪያ መሐመድ "ዛሬ ገና ነው ቢሮ የተከፈተው፤ ቅዳሜ ዝግ ነው እዚህ..." ሲሉ መልሰዋል።
የአምባሳደሩ ተወካይ ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን አሁን የት ሆስፒታል እንደሚገኙና የጤንነታቸውን ሁኔታ እንዲገልጹ በቢቢሲ ተጠይቀው "ሁለቱ ኢትዯጵያዊየን ከየት እንደመጡና አሁን የት እንዳሉ ምንም መረጃ እንደሌላቸው ተናግረው እኛም ጉዳዩን እንደናንተው በሚዲያ ነው የሰማነው" ብለዋል።
"የሚመለከተውን መሥሪያ ቤት ጠይቀናል፤ አዲስ መረጃ ካለ እንነግራችኋለን፤ ለጊዜው መረጃ አልሰጡንም" ብለዋል።
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር 13 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ኮቪድ-19 ተጠቂዎች መሆናቸውን ደርሼበታለሁ ብሎ ነበር።
ከነዚህ ውስጥ ሦስቱ የራሱ ዜጎች ናቸው። የተቀሩት ከሞሮኮ፣ ቻይና፣ ሕንድ፣ ታይላንድ፣ ሳኡዲና ኢትዯጵያ መሆናቸው ተዘግቦ ነበር።
ከ13ቱ ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የጤናና የበሽታዎች መከላከል ሚኒስትር ከትናንት በስቲያ አርብ ዕለት ነበር ያሳወቀው። የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግን 'ለጊዜው ዜጎቹ ስላሉበት ሁኔታ ምንም መረጃ የለኝም' ነው የሚለው።

የፎቶው ባለመብት, Ministry of health and prevention/FB
በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ከአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሌላ የዱባይ ቆንጽላ መረጃ ካለው በሚል ቢቢሲ ወደዚያው የደወለ ሲሆን "ጉዳዩ አቡዳቢ ስለሆነ እኛ ምንም የምናውቀው ነገር የለም፤ 'እዚያው ጠይቁ' የሚል ምላሽ አግኝቷል።
ሁለቱ ኢትዯጵያዊያን ስላሉበት ሁኔታ በተመለከተ የአቡዳቢም ሆነ የዱባይ ኤምባሲ ቢሮዎች ለጊዜው መረጃ የለንም ቢሉም የኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ሁኔታውን እየተከታለ መሆኑን ገልጾ ሁለቱ ኢትዮጵያዊያን ለዓመታት እዚያው ይኖሩ የነበሩና በቅርቡ ወደየትኛውም አገር ጉዞ እንዳላደረጉ አረጋግጫለሁ ብሏል።
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ሚኒስትር ዲኤታ ሊያ ታደሰ ዛሬ (እሑድ) ማለዳ በትዊተር ሰሌዳቸው ተያዙ ከተባሉት 13 ሰዎች 2ቱ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን አረጋግጠው ኢትዮጵያውያኑ ለረዥም ዓመታት የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ የኖሩና በቅርቡ ወደየትኛውም ሃገር ያልተጓዙ ናቸው ብለዋል።
ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ደግሞ ከሁለቱ መካከል አንደኛው ግለሰብ ድጋሚ ተመርምረው ቫይረሱ እንደሌለባቸው ተረጋግጧል ሲሉ በትዊተር ገፃቸው አሳውቀዋል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
የተበባበሩት አረብ ኢምሬትስ እስካሁን በአገሬ 45 ሰዎች በኮሮና መያዛቸውን ደርሼበታለሁ ብላለች። ከ45ቱ በተጨማሪ 18 አዳዲስ ተጠቂዎች እንደተገኙ የዓለም ጤና ድርጅት ድረ ገጽ ያትታል።
በአሁኑ ሰዓት የኮሮና ተጠቂዎቹ ተለይተው ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሆነም ተዘግቧል።
ይህን ተከትሎ ከዛሬ ጀምሮ ትምህርት ቤቶች ለአራት ሳምንታት እንዲዘጉ ትዕዛዝ ተላልፏል። አልፎም ዜጎቿ ወደ ሌሎች ሃገራትን የሚያደርጉትን ጉዞ ገታ እንዲያደርጉ አሳስባለች።













