ልዑል ሃሪና ሜጋን ያለባቸውን ዕዳ ሠርተው እንደሚከፍሉ አስታውቀዋል

የእንግሊዙ ልዑል ሃሪና ባለቤቱ ሜጋን ማርክል ከዚህ በኋላ የቤተ-መንግሥት መጠሪያቸውን እንደማይጠቀሙ አሳውቀዋል። ባልና ሚስቱ ከዚህ ባለፈ የቤተ-መንግሥት ገንዘብ እንደማይጠቀሙም ጠቁመዋል።

መግለጫውን ያወጣው የእንግሊዝ ንጉሳዊያን መቀመጫ የሆነው የባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት ነው። አልፎም ጥንዶቹ ከዚህ በኋላ ንግሥቷን እንደማይወክሉ ተሰምቷል።

ጥንዶቹ እንግሊዝ ሲመጡ የሚያርፉበት ፍሮግሞር ጎጆ ለተሰኘው ቤት የወጣውን 2.4 ሚሊዮን ፓውንድ ሠርተን እንከፍላለንም ብለዋል።

'የሰሴክስ ዱክ እና ዱቸስ' የሚል መጠሪያ ያላቸው ሃሪና ሜጋን የቤተ-መንግሥት ሥልጣንና ኃላፊነት በቃኝ ካሉ ወዲህ መነጋገሪያነታቸው ይልቁኑ ጨምሯል።

ጥንዶቹ በወደፊት ዕጣ-ፈንታቸው ዙሪያ ከንግሥቲቱ ጋር ከመከሩ በኋላ ነው እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ተብሏል።

ንግሥቲቱ በለቀቁት መግለጫ ላይ 'ከወራት ውይይት በኋላ ለልጅ ልጄ እና ቤተሰቡ የሚበጅ ውሳኔ ላይ በመድረሳችን ደስተኛ ነኝ' ሲሉ ተደምጠዋል። 'ሃሪ፣ ሜጋንና ልጃቸው አርቺ ሁሌም ተወዳጅ የቤተሰቡ አባላት ሆነው ይቀጥላሉ' ይላል መግለጫው።

መግለጫው ላይ እንደሚመለከተው የእንግሊዟ ንግሥት ሃሪና ሜጋንን አመሰግነዋል። በተለይ ደግሞ 'ሜጋን ከቤተሰቡ ጋር ለመቀላቀል ጊዜም አልወሰደባት' ብለዋል።

ቤተ-መንግሥቱ ባወጣው ሌላ መግለጫ ጥንዶቹ የልዕልና ማዕረጋቸውን ከዚህ በኋላ መጠቀም እንደማይችሉ አሳውቋል። ነገር ግን ይህ ብዙዎችን ግራ ያጋባ ሆኗል። ምክንያቱ ደግሞ ጥንዶቹ የቤተ-መንግሥት ኃላፊነት በቃን እንጂ የቤተሰብ አባልነታችን ይገፈፍ አላሉምና ነው።

የጥንዶቹ መፃኢ ዘመን ምን ሊመስል ይችላል የሚለው አሁንም ማነጋገሩን ቀጥሏል። ገንዘብ ከየት ያገኛሉ? የግል ጠባቂ ማን ይመድብላቸዋል? እና የመሳሰሉት። ቤተ-መንግሥቱ በመሰል ጉዳዮች ላይ አስተያየት መስጠት እንደማይችል አሳውቋል።

ሃሪና ሜጋን ከጋብቻ በፊትም ሆነ ከጋብቻ በኋላ በእንግሊዝ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ እጅግ እየተፈተኑ እንደሆነ ሲጠቅሱ ነበር። የልዕልት ዲያና ልጅ የሆነው ልዑል ሃሪ 'ሚስቴ እንደ እናቴ ዓይነት ዕጣ ፈንታ እንዳይገጥማት እሰጋለሁ' ሲልም ተደምጦ ነበር።