የአውስትራሊያ ነባር ብሔረሰቦች ጫካ እንዲቃጠል የሚፈልጉት ለምን ይሆን?

አቦርጂናሎች የአውስትራሊያ ጫካ እንዲቃጠል የሚፈልጉት ለምን ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለሺህ ዘመናት የአውስትራሊያ ነባር ብሔረሰቦች ጫካ በማቃጠል ይታወቃሉ።

አውስትራሊያ በአውሮጳውያን ከመወረሯ በፊት የነበረ ባህል ነው፤ 'ባሕላዊ ቃጠሎ' ሲሉ ይጠሩታል።

ነገር ግን በዕቅድ ነው የሚቃጠለው፤ የእሣቱም ቁመት ከጉልበት የሚበልጥ አይደለም። የተመረጡ ሥፍራዎችን ይዞ የሚቀጣጠል ነው።

አሁን አውስትራሊያን በጭንቀት ሰቅዞ የያዛት ሰደድ እሣት አምና ሲጀምር ይህን ባሕላዊ መንገድ መጠቀም አስፈላጊ ነበር የሚሉ ድምፆች ከየቦታው መሰማት ጀመሩ። ነገር ግን ሃሳቡ መደመጥ የጀመረው ዘግይቶ ነበር።

ሻኖን ፎስተር የተሰኙ የአቦርጅናሎችን ባሕል በማጥት የሚታወቁ ሴት «አጫጭር ዛፎች [ቡሽ] መቃጠል አለባቸው» ይላሉ።

«ይህ መንገድ 'ሃገር ሳትቃጠል በቅጠል' ለመከላከል የሚደረግ ሙከራ ነው። እኛ አቦርጅናሎች በዚህ እንታወቃለን። ከሃገራችን ስለምንወስደው ብቻ ሳይሆን ለሃገራችን ስለምናበረክተውም እናስባለን።»

አቦርጅናሎችና ሃገር

በአቦርጅናሎች ዘንድ ሃገር እንደ ሰው ትመሰላለች። «መሬት እናታችን ናት። በሕይወት ታኖረናለች» ይላሉ አጥኚዋ ሻኖን። ቅድመ ቃጠሎ ደግሞ አደጋ ከመምጣቱ በፊት በአቦርጅናሎች የሚከወን መከላከያ መንገድ ነው።

'ዘመናዊ ነን' የሚሉ ሰዎች አደጋ ከመከሰቱ በፊት የሚያከውኑት ተግባር እየሠራ አይመስለኝም ይላሉ ምሁሯ።

ሻኖን ፎስተር

የፎቶው ባለመብት, CATHERINE MCLACHLAN

የምስሉ መግለጫ, ሻኖን ፎስተር ጥበብን ከአያቶቻቸውን እንደቀዱ ይናገራሉ

«ዘመናዊው መንገድ ሁሉን ነገር እያጠፋ ነው። በብልሃት እየተሠራ አይመስለኝም። ነባር ብሔረሰቦች ጫካውን የሚያውቁትን ያህል ከተሜዎች ያወቁት አልመሰለኝም።»

«ንበረት አይተነፈስም፣ አይበላም፣ አይጠጣም። ያለ ሃገር የሰው ልጅ ከንቱ ነው።»

ባሕላዊ ቃጠሎ የጫካውን ቅኝት ተከትሎ የሚደረግ ነው። በቃጠሎው ወቅት ከጫካው የሚሸሹ ተሳቢና ባለ አራት እግር እንስሳት የአቦርጅናሎች እራት ይሆናሉ። ቃጠሎው የሚፈጥረው አመድ ፖታሺዬም ወደ ተሰኘው ኬሚካል ተቀይሮ ለመሬቱ እንደ ማዳበሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል የአካባቢው ሰዎች ይናገራሉ።

ባሕላዊ ቃጠሎ ያልተካሄደለት ጫካ ማለት ፀጉሩ እንዳልተከረከመ ሕፃን ልጅ ማለት ነው' እንክብካቤ ይጠይቃል ይላሉ ሻኖን። አክለውም ታላላቆቿ ይህ ቀን ሊመጣ እንደሚችል ጥንቃቄ ቢሰጡም የሰማቸው የለም ይላሉ።

አውስትራሊያ የተሰባጠረ ምድራዊ አቀማመጥ ያላት ሃገር ናት። ከቦታ ቦታ የተለያየ መልክ ያለው ምድር አላት። አንዳንድ ሥፍራዎች ባሕላዊውን የጫካ አያያዝ ከዘመናዊው ጋር አሳልጠው ይጠቀማሉ። ብዙዎች ግን ሃገር-በቀሉን መንገድ ለመጠቀም ዝግጁ አይመስሉም።

«ሰሜናዊው የአውስትራሊያ ክፍል እንዴት አድርጎ ባሕላዊውን መንገድ እንደሚጠቀምበት ማየት ይቻላል። ደቡባዊው ክፍል ግን ወጣ ገባ ነው።»

አውስትራሊያ ቅኝ ከተገዛችበት 1788 ጀምሮ ባሕላዊ ቃጠሎ እየጠፋ ቢመጣም አሁን አሁን እንደ አዲስ እያበበ ነው። እርግጥ ነው ባሕላዊው ቃጠሎ የራሱ የሆኑ ችግሮች አሉበት ብለው የሚያምኑ አሉ። ተግባራዊ መደረግ ያለበት ሁሉ ቦታ አይደለም ይላሉ።

የአውስትራሊያ ሰደድ እሣት ከ10 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ያቃጠለ ሲሆን 27 ሰዎችን ገድሏል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዱር እንሳስትም ሰለባ ሆነዋል።