ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እግራቸው አሜሪካ ልባቸው አፍሪካ ያለ የሆሊውድ ተዋንያን
አፍሪካ አሜሪካዊው ራፐር ሉዳ ክሪስ ሰሞኑን አፍሪካዊ ዜግነት አግኝቷል። በእውነተኛ ስሙ ክርስቶፈር ብሪያን ብሪጅስ በመባል የሚታወቀው ሉዳክሪስ አፍሪካዊ ዜግነት በቅርቡ ያገኘ የሆሊውድ ተዋናይ ነው።
የሉዳክሪስ ውሃ አጣጭ ጋቦናዊት ስትሆን እናቱና ሁለት ሴት ልጆቹም ጋቦናዊ ዜግነት አግኝተዋል።
በሆሊውድ ከፍ ካለ የዝና ማማ ላይ የሚገኘው ሉዳ ክሪስ፣ በነዳጅ ሐብቷ ከበለፀገችው ጋቦን ምን ፈልጎ ነው? የሚል ደፋር ጠያቂ ቢመጣ፣ የእርሱ መልስ 'ወደ አፍሪካዊ ማንነቴ መመለስ ፈልጌ' የሚል ይሆናል።
ከሉዳክሪስ በፊት ግን በርካታ የሆሊውድ ተዋንያን አፍሪካዊ ዜግነት አግኝተዋል።
ሳሙኤል ኤል ጃክሰን የጋቦንን ፓስፖርት ያገኘው የከየት መጣሁ ጥያቄን ለመመለስ በተሰራው ዘጋቢ ፊልም ላይ ተሳትፎ የዲኤን ኤ ምርመራ ካደረገ በኋላ ነበር።
ታዲያ የዘር ግንዱ ወደኋላ ሲቆጠር በደሙ ውስጥ ጋቦን ገነን ብላ ስለተገኘች ጋቦንም ሳታቅማማ ፓስፖርቷን ጀባ ብለዋለች።
ጋቦን ብቻ አይደለችም ለአፍሪካ አሜሪካዊያን ዜግነት የሰጠችው።
በግንቦት ወር ኮሜዲያንና ተዋናይት የሆነችው ቲፋኒ ሐዲሽ ወደ ኤርትራ ተጉዛ ዜግነት አግኝታለች። በዚህ ተግባሯ አንዳንዶች የኤርትራን አምባገነን መንግሥት ትደግፋለች በሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ባለፈው ሕዳር ወርም ጋና ለ126 አፍሪካ አሜሪካውያን እንዲሁም አፍሮ ካሪቢያን ዜግነትን ሰጥታለች። ይህንን ያደረኩት አፍሪካውያን በባርነት ተወስደው ሰሜን አሜሪካ እግራቸው የረገጠበትን 400ኛ ዓመት በማሰብ ነው በማለት 'የመመለስ ዓመት' በሚል ስም ዜግነት መስጠቷን ይፋ አድርጋለች።
እንግሊዛዊው ታዋቂ የፊልም ተዋናይ ኢድሪስ ኤልባም የሴራሊዮን ዜግነት ያገኘው ባለቀው የፈረንጆች ዓመት የመጨረሻ ወር ላይ ነበር።
የኤድሪስ ኤልባ አባት ሴራ ሊዮናዊ ሲሆኑ ዜግነቱን ያገኘው ለመጀመሪያ ጊዜ ሀገሪቱን በረገጠበት ወቅት ነበር።
ኢድሪስ በወቅቱ "ከአገሬ ላገኘው የምችለው ትልቁ ክብር ነው" ሲል ነበር የተሰማውን ለቢቢሲ የገለፀው።
ለአፍሪካ አዲስ ያልሆነው ኢድሪስ ስለአፍሪካ ፊልም መስራቱን አፍሪካ ውስጥ ፊልም መቅረፁን ከጠቀሰ በኋላ "ሴራሊዮን ግን በልቤ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላት" በማለት የቤተሰቦቹ አገር መሆኗን ገልጿል።
በዚህ ዓመት በጋና የተዘጋጀው አፍሮፌስት ክብረ በዓል ላይ ለመገኘት ታዋቂዋ ሞዴል ናኦሚ ካምቤል፣ ተዋናይቷ ሉፒታ ኒያንጎ፣ ድምጻዊ ኤኮን፣ የቢዮንሴ እናት ቲና ኖውልስ ላውሰን ቀጠሮ ይዘዋል።