የተባበሩት መንግሥታት የቺሊ ፖሊሶች ሰብዓዊ መብት ጥሰዋል አለ

በቅርቡ ከተቀሰቀሰው የቺሊ ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ፤ የተባበሩት መንግሥታት የአገሪቱ ፖሊሶችና ወታደሮች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል አለ።

ድርጅቱ፤ በአራት ግለሰቦች ግድያ የጸጥታ ኃይሎች እጅ እንዳለበት በምርመራ ደርሼበታለሁ ብሏል።

345 ሰዎች ከተረፈ ምርት የተሠራ ፕላስቲክ ተወርውሮባቸው አይናቸው መጎዳቱን፤ ሌሎች ደግሞ ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸውም ድርጅቱ አመልክቷል።

ባለፈው ኅዳር አጋማሽ ከታገቱት 28,000 ሰዎች መካከል 1,600 ያህሉ ለቅድመ ምርመራ እንደተያዙ ናቸው።

የቺሊ ተቃዋሚዎች ማኅበራዊ ለውጥ እንዲመጣ እንዲሁም የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ማሻሻያ እንዲደረግበት ጠይቀዋል።

ተቃውሞ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ ቢያንስ 26 ሰዎች ተገድለዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ክፍል እንዳሳወቀው፤ የቺሊ መንግሥት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ከ4,900 በላይ ናቸው ቢልም፤ ቁጥሩ ከዛም ሊጨምር እንደሚችል የገለጹ አካላት አሉ።

የተባበሩት መንግሥታት፤ 113 አካላዊ እንግልት የደረሰባቸው ሰዎችን ጉዳይ መዝግቧል። ፖሊሶች፤ 24 ሴቶችና ወንዶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ማድረሳቸውን አሳውቋል። በተጨማሪም መሣሪያና አስለቃሽ ጭስ ያላግባብ ጥቅም ላይ እንደዋሉም ተመልክቷል።

የድርጅቱ የቡድን መሪ፤ ኢማ ጉሬስ ዴላጋዶ እንደተናገሩት፤ ፖሊሶች ከፍተኛ ጭቆና ማሳደራቸውን ደርሰውበታል።

በቺሊ መዲና ሳንድያጎ የሕዝብ መጓጓዣ ዋጋ ይጨምራል መባሉን ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ በመላው አገሪቱ ተሰራጭቷል። ኢ-ፍትሐዊነትን፣ የህክምና እና የትምህርት ዋጋ መናርን በመቃወምም ሕዝባዊ ሰልፉ ቀጥሏል።

የፖሊሶች ጭካኔ የተሞላ እርምጃ የሕዝቡን ቁጣ ያጋጋለው ሲሆን፤ ፕሬዘዳንት ሰባስሽን ፒኔራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል።